የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን በዘር ማጥፋት ወንጀል የከሰሱት የምዕራብ ዳርፉር አስተዳዳሪ ተገደሉ
የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎችን በዘር ማጥፋት ወንጀል የከሰሱት የምዕራብ ዳርፉር አስተዳዳሪ ተገደሉ
የምዕራብ ዳርፉር አስተዳዳሪ የተገደሉት የሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይል የዘር ማጥፋት ወንደጀል ፈጽሟል የሚል ክስ ካቀረቡ ከአንድ ቀን በኋላ መሆኑን ቢቢሲ ዘግቧል።
ካሚስ አክባር የተባሉት አስተዳዳሪ በሰጡት የቴሌቪዥን መግለጫ በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች እና በአረብ ሚሊሻዎች የሚደርሰውን ጥቃት አለም አቀፉ ማህበረሰብ ጣልቃ ገብቶ እንዲያስቆም ጠይቀው ነበር።
በሱዳን ጦር እና በፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መካከል ከሁለት ወራት በፊት የተቀሰቀሰው ጦርነት በዳርፉር ያለውን የጎሳ ውጥረት አባብሶታል።
ጦርነቱ ባለው ሚያዚያ ከተቀሰቀሰ ወዲህ የተገደሉ ከፍተኛ ባለስልጣን የሚባሉ ናቸው።
በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲዘዋወሩ የነበሩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች የፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን መለያ የለበሱ የታጠቁ ቡድኖች አስተዳዳሪውን ሲይዙ ታይተዋል።
ነገርግን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ይህን የፈጸሙት ህገወጦች መሆናቸውን እና አክባርን ለማዳን ጥረት ማድረጉን ገልጿል።
በዳርፉር ግዛት ጥቁር አፍሪካዊያን እና የአረብ ማህበረሰብ አባለት ለረጅም ጊዜ የቆየ አለመግባባት ውስጥ ናቸው።
በሁለቱ ጎሳዎች መካከል ከባድ የሚባል ግጭት የተቀሰቀሰው ጥቁሮቹ መገለል ደርሶብና በሚል ከሁለት አስርት አመታት በፊት መሳሪያ በማንሳታቸው ነበር።
ጥቁሮቹ መሳሪያ ማንሳታቸውን ተከትሎ መንግስት ጃንጃውል በመባል የሚታወቀውን የአረብ ሚሊሻ አቋቁም ነበር።
ይህ የሚሊሻ ቡድን ግፎች እና ዘር ማጥፋት ፈጽሟል የሚል ክስ ቀርቦባቸው ነበር።
በሱዳን ጦርነቱ አሁንም እንደቀጠለ ነው።
ሁለቱ የሱዳን ተፋላሚ ኃይሎች በአሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ አደራዳሪነት ተኩስ እንዲያቆሙ ቢጠየቁም ሊስማሙ አልቻሉም።