ሜ/ጄኔራል ገብረ መድህን ፍቃዱ (ወዲ ነጮ) በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ
ወዲ ነጮ የተለያዩ በምቦችን ጨምሮ የሚሳይል መሳሪያዎችንም ለሕወሓት ጁንታ ሊልኩ ሲያዘጋጁ ነበር ተብሏል
ወዲ ነጮን ጨምሮ ከሕወሓት ጋር በማበር በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም አድርገዋል በሚል የተጠረጠሩ 17 የመከላከያ ሰራዊት አመራሮች ተይዘዋል
ሜ/ጄኔራል ገብረ መድህን ፍቃዱ (ወዲ ነጮ) በፖሊስ ቁጥጥር ስር ዋሉ
የሰሜን ዕዝ ከማዕከል ጋር የሚኖረው የመገናኛ ስርዓት እንዲቋረጥ በማድረግ በዕዙ ላይ በጁንታው የሕወሓት ቡድን ጥቃት እንዲፈጸም ሲያመቻቹ ነበሩ የተባሉ ጄኔራል መኮንኖች ከነ ግብረ-አበሮቻቸው ጋር በቁጥጥር ስር ዋሉ፡፡
የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን በሰጠው መግለጫ እንዳስታወቀው የመከላከያ ሰራዊት አባል ሆነው ኃላፊነታቸውን በመተው ፣ የጁንታው ቡድን ሴራ አካል በመሆን በሀገር ክህደት ወንጀል ተጠርጥረው ከተያዙት መካከል ጄነራል መኮንኖች ፣ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች እና ሌሎች የበታች ሹማምንቶች ይገኛሉ፡፡
ሜ/ጄኔራል ገብረ መድህን ፍቃዱ (ወዲ ነጮ) ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ምሽት ላይ የሰሜን ዕዝ ከማዕከል ጋር ያለው ግንኙነት ሙሉ በሙሉ እንዲቋረጥ በማድረግ ለተፈጸመው ጭፍጨፋ ምቹ ሁኔታ ፈጥረዋል በሚል ተጠርጥረው በፖሊስ ተይዘዋል፡፡
ሜ/ጄኔራል ገብረ መድህን ፍቃዱ ከለውጡ በፊት የአጋዚ ኮማንዶ እና ልዩ ኃይሎች አዛዥ የነበረ ነው፡፡ ለውጡን ተከትሎ ደግሞ የሰራዊቱ የመገናኛ መምሪያ ኃላፊ በመሆን ሲሰራ እንደነበር የፖሊስ መግለጫ ያመለክታል፡፡
ግንኙነት እንዲቋረጥ በማድረግ በዕዙ ላይ ጥቃት እንዲፈጸም ከማድረጉም በላይ ፣ የመገናኛ መሳሪያ ነው በማለት በውስጣቸው ቦምቦች እና የሚሳይል መሳሪያዎችን የያዙ 11 ሳጥኖችን ለሕወሓት ወደ ትግራይ ሊልክ ሲዘጋጅ ከተለያዩ የጦር መሳሪያዎች ጋር እጅ ከፍንጅ መያዙንም ፖሊስ አስታውቋል፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና የፌዴራል ፖሊስ ባደረጉት ክትትል እና ባካሔዱት ኦፐሬሽን ሜ/ጄኔራል ገብረ መድህን ፍቃዱን ጨምሮ በድምሩ 17 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡ በቀጣይነትም ሌሎች ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር የማዋል ስራ እንደሚቀጥል ፌዴራል ፖሊስ አስታውቋል፡፡ ዘገባው የኢቲቪ ነው፡፡