“በሀገሪቱ እና በቀጣናው መረጋጋትን ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት መከበር አለበት”-የአፍሪካ ህብረት
ሕግ የማስከበር እርምጃው “ወንጀለኛው ጁንታ ትጥቅ ሲፈታ” እንደሚያበቃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልጸዋል
በኢትዮጵያ ላለው ቀውስ ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ ሁሉም አካላት እንዲወያዩ የአፍሪካ ህብረት ጠይቋል
“በሀገሪቱ እና በቀጣናው መረጋጋትን ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ ሕገ-መንግስታዊ ስርዓት መከበር አለበት”-የአፍሪካ ህብረት
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት በኢትዮጵያ ያለው ወታደራዊ ግጭት መባባሱ እንዳሳሰባቸው ገለጹ፡፡
ሊቀመንበሩ በሀገሪቱ እና በቀጣናው መረጋጋትን ለማረጋገጥ በኢትዮጵያ ህገ-መንግስታዊ ስርዓት መከበር እንዳለበት ፣ የግዛት እና የህዝቦች አንድነት እንዲሁም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ ብሄራዊ ሉዓላዊነት መከበር እንዳለበት የአፍሪካ ህብረት እንደሚያምን በአጽንኦት አረጋግጠዋል፡፡
ሊቀመንበሩ ግጭቶች በፍጥነት እንዲቆሙ የጠየቁ ሲሆን ሁሉም አካላት ሰብዓዊ መብቶችን እንዲያከብሩና የዜጎችን ደህንነት እንዲያረጋግጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ ለሀገር ጥቅም ሲባል ሰላማዊ መፍትሄ ለመፈለግ ሁለቱም አካላት እንዲወያዩም ነው ያሳሰቡት፡፡
ሰላም እና መረጋጋትን ለማስፈን በኢትዮጵያውያን መካከል የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ የአፍሪካ ህብረት ዝግጁ እንደሆነም ሊቀመንበሩ አረጋግጠዋል፡፡
የትግራይ ክልል ኮሙኒኬሽን ቢሮ በፌስ ቡክ ገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ዶ/ር ደብረጺዮን ገብረ ሚካኤል ፣ በኢትዮጵያ የተፈጠረውን ችግር በድርድር ለመፍታት ሁሉንም አካላት ያሳተፈ ውይይት እንዲካሔድ የአፍሪካ ሕብረት ኃላፊነቱን እንዲወጣ መጠየቃቸውን ገልጿል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ ለወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀመንበር ጥቅምት 27 ቀን 2013 ዓ.ም ደብዳቤ ስለመጻፋቸውም ነው ቢሮው የጠቆመው፡፡
ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ መንግስት ድርድር ለማድረግ “ጊዜው ማለፉን” እና “በትግራይ ክልል የሚገኙ ወንጀለኞች” በህግ ጥላ ስር እስኪውሉ ህግን ለማስከበር የሚወሰደው የኃይል እርምጃ እንደሚቀጥል ገልጿል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) የቀረበውን የሽምግልና ጥሪም አለመቀበላቸው መዘገቡ ይታወቃል፡፡
የኢጋድ የወቅቱ መሪ የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ በ4 የተለያዩ ጊዜያት ስልክ በመደወል የኢትዮጵያ አቻቸውን ለማግባባት ቢጥሩም ሊሳካላቸው አልቻለም ነው የተባለው፡፡
ከሃምዶክን ቢሮ ያገኘውን መረጃ በመጥቀስ የዘገበውን ሂቃያት ጋዜጣን ዋቢ አድርጎ ፣ ሱዳን ትሪቢውን በድረ ገጹ እንዳሰፈረው ዘገባ ከሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጉዳዩ ዓለም አቀፋዊ መልክ ሊይዝ የማይገባው የሃገር ውስጥ ጉዳይ ነው ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ በትዊተር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ ደግሞ ሕግ የማስከበር እርምጃው “ወንጀለኛው ጁንታ ትጥቅ ሲፈታ፣ በክልሉ ቅቡልነት ያለው አስተዳደር ሲቋቋም እና የሸሹት ለፍርድ ሲቀርቡ ይጠናቀቃል” ብለዋል፡፡
በትግራይ ክልል እየተከናወነ የሚገኘው ህግን የማስከበር ስራ በተያዘው እቅድ መሰረት እየተከናወነ እንደሚገኝም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል። ይህም በፍጥነት እንደሚጠናቀቅም ነው የገለጹት፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትናንትናው ዕለት ደግሞ “የሕግ የነላይነትን ለማረጋገጥ የምንወስደው እርምጃ ወንጀለኞችን ለፍትህ በማቅረብ ሰላምና መረጋጋትን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማረጋገጥ ያለመ ነው” ያሉ ሲሆን “ወዳጆቻችን ስጋታቸውን በመግለጻቸው ኢትዮጵያ ታመሰግናለች” ማለታቸው ይታወቃል፡፡
በአየር ኃይልም ጭምር ሕግን ለማስከበር የሚወሰደው እርምጃ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል፡፡