“ከግጭቱ ዋዜማ የትግራይ ክልል መሪ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተደዋውለው ነበር” - አምባሳደር ሬድዋን
አፈግፍጎ የነበረው ሰራዊት እንደገና ራሱን በማሰባሰብና በማደራጀት በሽራሮ እና በሌሎችም አቅጣጫዎች እየተጠጋ እንደሚገኝም ገልጸዋል
“የጦርነት ፊልም እንኳን ሊያዩ የማይገባቸው ታዳጊዎች ጭምር ናቸው በግጭቱ እየተሳተፉ ያሉት”
“ከግጭቱ ዋዜማ የትግራይ መሪ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተደዋውለው ነበር”- አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የመረጃ ፍሰት ቃል አቀባይ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ወቅታዊ ሃገራዊ ሁኔታዎችን በማስመልከት መቀመጫቸውን አዲስ አበባ ላደረጉ የውጭ መገናኛ ብዙሃን ገለጻ አደረጉ፡፡
“ከግጭቱ ዋዜማ የትግራይ ክልል መሪ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ተደዋውለው ነበር” ያሉት ቃል አቀባዩ “ሁኔታውን በቀላሉ እንደሚይዙት እና በንግግር ሊፈቱት እንደሚችሉ ተነጋግረው ነበር” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩም ይህንኑ ታሳቢ በማድረግ በአዲስ የተቀየረውን ብር ወደ ትግራይ ለመላክ እና ክልሉ የእለት ተዕለት የቢዝነስ እንቅስቃሴ ለመደገፍ ቃል ገብተዋል፡፡
ሆኖም በዚያው ቀን ምሽት በክልሉ በሚገኘው የሃገሪቱ ጦር የተለያዩ ጣቢያዎች ላይ ድንገተኛ ጥቃት መከፈቱን ነው የገለጹት፡፡
ጥቃቱ በተመረጡ የሰራዊቱ አካባቢዎች ላይ በተመሳሳይ ሰዓት የተፈጸመ ነው፡፡
በዚህም ተዋጊ ኃይል የሌለው የሰራዊቱ የመቀሌ ካምፕ በቀላሉ በጥቃት ፈጻሚዎቹ እጅ ሲገባ ሌሎች የሰራዊቱ አካባቢዎች ግን የተከፈተባቸውን ድንገተኛ ጥቃት ለመከላከል እና ወደተለያዩ አካባቢዎች ለማፈግፈግ ሞክረዋል፡፡
“ሌሎች አካላት መጥተው እስከሚታደጉት ድረስም ሰራዊቱ ለሶስት ቀናት በከበባ ውስጥ ሆኖ ሲከላከል ቆይቷል” እንደ ቃል አቀባዩ ገለጻ፡፡
“ጥቃቱ በተፈጸመ ማግስት የክልሉ መሪዎች ሊያጠቃቸው የሚመጣን የትኛውንም አካል ለመከላከል ብቻም ሳይሆን በተሻለ ለማጥቃት የሚያስችል አቅም እንዳላቸው መግለጻቸው ከሰራዊቱ የዘረፏቸውን ሮኬቶች እና ሚሳዔሎች በመተማመን ነው” ያሉት ቃል አቀባዩ ጦር መሳሪያዎቹ ተመልሰው ለጥፋት በማይችሉበት ሁኔታ እንዲወድሙ መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ይልቁንም “ይህ ግጭቱን ማን ቀድሞ እንደጀመረው አመላካች” እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
አዲስ አበባ እና ደብረ ዘይትን ለማጥቃት የሚያስችል ተተኳሽ ጦር መሳሪያ እንዳላቸው መግለጻቸው ከእውነት የራቀ ውሸት እንደሆነም ቃል አቀባዩ ተናግረዋል፡፡
የፌዴራል መንግስቱም በሶስት ግልጽ ዓላማዎች ላይ በመመስረት እርምጃዎችን መውሰድ ጀምሯልም ብለዋል፡፡
ዓላማዎቹም “ዘርፈው የያዟቸው ሮኬትን መሰል ከባባድ ጦር መሳሪያዎች ተመልሰው ህዝብን ለማጥቃት እንዳይውሉ የማድረግ፣ ህግና ህገመንግስታዊ ስርዓትን የማስከበር እና ወንጀለኞቹን ለህግ የማቅረብ” ናቸው፡፡
መንግስት ዘመቻውን በአጭር ጊዜ በአነስተኛ የጉዳት መጠን እና የንጹንን ደህንነት ባስጠበቀ መልኩ ለማጠናቀቅ ጥረት በማድረግ ላይ ይገኛልም ብለዋል አቶ ሬድዋን፡፡
“በዘመቻዎቹ ሰራዊቱ አዋሳኝ የሱዳን አካባቢዎችን ጨምሮ ሌሎችንም ቦታዎች ለመቆጣጠር ችሏል” ያሉም ሲሆን አፈግፍጎ የነበረው ሰራዊት እንደገና ራሱን በማሰባሰብና በማደራጀት በሽራሮ እና በሌሎችም አቅጣጫዎች እየተጠጋ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡
ከጋዜጠኞች ለቀረቡላቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት ቃል አቀባዩ በግጭቱ የደረሱ ጉዳቶችን በዝርዝር ለማስቀመጥ የሚያስችሉ መረጃዎች ገና በመጠናቀር ላይ እንደሚገኙም ነው የተናገሩት፡፡
“የጦርነት ፊልም እንኳን እንዲያዩ ሊፈቀድላቸው የማይገቡ ታዳጊዎች ናቸው ተሰልፈው እየተዋጉ ያሉት” ቃል አቀባዩ “በክልሉ በነበረው ሰራዊት ላይ የደረሰውን ጉዳት ለማወቅ የነበረው ሰብዓዊ እና የመሳሪያ ኃይል ተቆጥሮ ልዩነቱ መታወቅ እንዳለበት” ገልጸዋል፡፡
መንግስት ቀደም ሲል የተገለጹትን ዓላማዎች ሳያሳካ ምንም ዓይነት የመደራደር ፍላጎት እንደሌለውም አቶ ሬድዋን አስታውቀዋል፡፡