የፌደራል መንግስት እና ህወሃት የፖለቲካ ውይይት ማካሄድ ጀመሩ
በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የተመራ የፌደራል መንግስት ልኡክ መቀሌ ገብቷል
ጠ/ሚ አቢይ ከህወሓት አመራሮች ጋር በጥር ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ መምከራቸው ይታወሳል
የፌደራል መንግስት እና ህወሃት የፖለቲካ ውይይት ማካሄድ ጀመሩ።
በብልጽግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዝዳንት አደም ፋራህ የተመራ የፌደራል መንግስት ልኡክ መቀሌ ገብቷል።
የትግራይ ቴሌቪዥን እንደዘገበው ልኡኩ መቀሌ አሉላ አባነጋ አውሮፕላን ማረፊያ ሲደርስ የህውሃት ሊቀመንበር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል (ዶ/ር) አቀባበል አድርገውለታል።
የመከላከያ እና የትራንስፖርትና ሊጂስቲክ ሚኒስትሮችን ያካተተው የፌደራል መንግስት ልኡክ ከህወሃት እና ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባለስልጣናት ጋር ምክክር ማድረግ ጀምረዋል ነው የተባለው።
የፌደራል መንግስቱ እና ህወሃት የሁለት አመቱን ደም አፋሳሽ ጦርነት ለመቋጨት በፕሪቶሪያ በደረሱት ስምምነት መሰረት በፍጥነት ፖለቲካዊ ውይይት መጀመር ቢኖርባቸውም በተለያዩ ምክንያቶች ዘግይቷል።
ሁለቱም ወገኖች በመቀሊ ምክክር ሲጀምሩ የፖለቲካዊ ንግግሩ በመደበኛነት እንዲቀጥል መስማማታቸው ተገልጿል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጥር ወር መጨረሻ ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከህወሃት ሊቀመንበር ዶክተር ደብረጺዮን ገብረሚካኤል ጋር ለመጀመሪያ ጊዜ በአዲስ አበባ ፊት ለፊት መገናኘታቸው ይታወሳል።
በዚህ ምክክርም ሁለቱም አካላት የፖለቲካ ውይይት ለመጀመር መስማማታቸው አይዘነጋም።
የፕሪቶሪያው ግጭት የማቆም ስምምነት ከተፈረመ በኋላ በርካታ ለውጦች ቢኖሩም በአፈጻጸሙ ረገድ የሚነሱ ቅሬታዎች አሉ።
የፌደራል መንግስት በስምምነቱ መሰረት የህወሓት ታጣቂዎች ትጥቅ አልፈቱም የሚል ቅሬታ ያቀርባል።
የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር በበኩሉ በአማራ እና ኤርትራ ሃይሎች የተያዙ አካባቢዎች ወደ ቀደመ ይዞታቸው (ትግራይ) እንዲመለሱና ተፈናቃዮችም ወደ ቀያቸው ይመለሱ የሚለው በስምምነቱ የተካተተ ነጥብ ተፈጻሚ አልሆነም በሚል በተደጋጋሚ ወቀሳውን አቅርቧል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ሰብአዊ ድጋፍ በበቂ ሁኔታ እየደረሰ አይደለም፤ በትግራይ ከ77ቱ የከፋ ድርቅ አንዣቧል ማለቱን ተከትሎም የፌደራል መንግስት ለመጀመሪያ ጊዜ በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ ትችት መሰንዘሩ ይታወሳል።
የፌደራሉ መንግስት የአማራ እና ትግራይ ክልሎችን በሚያዋስኑ አካባቢዎች መከላከያ በማስገባት የህዝበ ውሳኔ ለማድረግ መታቀዱን ገልጿል፤ ከሰብአዊ ድጋፍ ጋር ተያያዞ የሚቀርቡ ክሶችንም በተደጋጋሚ ውድቅ አድርጓል።
በጥር ወር መጨረሻ በአዲስ አበባ ከተካሄደው ምክክር በኋላ ለዘብ ያለ የሚመስለውን የቃላት ልውውጥ በመቀሌ የተጀመረው ፖለቲካዊ ውይይት ይበልጥ ያጠናክረዋል ተብሎ ይጠበቃል።