በኢትዮጵያ በኩል፤ ከብራዚል ወደ ዱባይ እና ናይጀሪያ አደንዛዥ እጾችን ሊያዘዋውሩ የነበሩ የውጭ ዜጎች ናቸው በቦሌ አየር ማረፊያ የተያዙት
ፌደራል ፖሊስ በቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ከብራዚል የተነሱ አደገኛ እፅ አዘዋዋሪዎች ያዘ፡፡
መነሻቸውን ብራዚል ሳኦፖሎ መዳረሻቸውን ደግሞ ዱባይና ናይጄሪያ በማድረግ በአውሮፕላን ሲጓዙ የነበሩ የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎች በትላንትናው ዕለት በኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ አባላት በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡
የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎቹ ሁለት ናይጄሪያዊያንና አንዲት ብራዚላዊት ሲሆኑ በቦሌ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ በተደረገባቸው ፍተሻ እጅ ከፍንጅ መያዛቸውን ኢንስፔክተር አዲሱ ባለሚ ገልጸዋል፡፡
ግለሰቦቹ አደገኛ ዕፁን በውስጣዊ የሻንጣ አካል በመደበቅና ውጠው በሆዳቸው በመያዝ ለማሳለፍ ሙከራ ቢያደርጉም የፌደራል ፖሊስ ፍተሻ በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
በቁጥጥር ስር ከዋሉት ሶስት የአደገኛ ዕፅ አዘዋዋሪዎቹ መካከል በብራዚላዊቷ ላይ በተደረገ ፍተሻ ከ13 ኪሎግራም በላይ የሚመዝን 666 ጥቅል ፍሬና በዱቄት መልክ የተዘጋጀ ከ17 ኪሎግራም በላይ የሚመዝን 11 እሽግ ኮኬይን የተሰኘ አደገኛ ዕፅ በሻንጣዋ ይዛ መገኘቷን አረጋግጠዋል፡፡
ሁለቱ ናይጄሪያዊያን አደገኛ ዕፁን በሆዳቸው ይዘው ሊያዘዋውሩ እንደሚችሉ በመጠራጠር በፌደራል ፖሊስ ሆስፒታል በተደረገላቸው የኤክስ ሬይ ምርመራ የተገኘባቸው ሲሆን 1 ሺህ 650 ግራም የሚመዝን 83 ፍሬ ኮኬይን ከሆዳቸው እንዲወጣ መደረጉ ተገልጿል፡፡
ግለሰቦቹ ሰዎችን ለወንጀል የሚያነሳሳ በመሆኑ እንዳይዘዋወር፣ እንዳይመረት እና በጥቅም ላይ እንዳይውል በህግ የተከለከለ አደገኛ ዕፅ ይዘው ሲያዘዋዉሩ በመገኘታቸው የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በአሁኑ ወቅት ግለሰቦቹን በቁጥጥር ስር በማዋል ተጨማሪ ምርመራ እያካሄደ መሆኑ ታውቋል፡፡