በቦሌ ክፍለ ከተማ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሀሰተኛ የአሜሪካ ዶላር ከነተጠርጣሪው መያዙን ፖሊስ አስታወቀ
በህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሪ ቁጥጥር ከፍተኛ የውጭ ገንዘቦች እና 15 ሚሊዮን ብር መያዙንም ፖሊስ ገልጿል
በገንዘብ ማጭበርበበር ስራ የተሳተፉ የውጭ ሀገር ዜጎች መያዛቸው ተገልጿል
በቦሌ ክፍለ ከተማ ከ2 ሚሊዮን በላይ ሀሰተኛ የአሜሪካ ዶላር ከነተጠርጣሪው መያዙን ፖሊስ አስታወቀ
በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ጉርድ ሾላ ሰፈረ ገነት ተብሎ በሚጠራው አካባቢ አንድ የውጭ ሃገር ዜግነት ያለው ግለሰብ ተከራይቶ በሚኖርበት ቤት ውስጥ ሃሰተኛ ዶላር እንደሚያዘጋጅ ጥቆማ መድረሱን የገለፁት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በመኖሪያ ቤቱ ውስጥ ከ2 ሚሊዮን 470 ሺህ በላይ የአሜሪካ ዶላር ከነተጠርጣሪው ተይዞ ምርመራ እየተጣራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በተመሳሳይ በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 13 ዛሜሌክስ ሆቴል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የውጭ ሃገር ዜግነት ያለው ግለሰብ “ከአንድ የአፍሪካ ሃገር ወደ ኢትዮጵያ በዲፕሎማቶች አማካይነት የሚገባ 5 ሚሊዮን ዶላር አለ” በማለት ሌላ ግለሰብን በማታለል ገንዘብ ለመውሰድ ሲሞክር የግል ተበዳይ ተጠራጥረው ለፖሊስ በሰጡት ጥቆማ እና ፖሊስ ባደረገው ክትትል ከጉዳዩ ጋር በተያያዘ ሁለት ተጠርጣሪዎችን እና በገንዘብ መጠን የተቆራረጠ ወረቀት በኤግዚቢትነት ይዞ ምርመራ እያጣራ እንደሚገኝ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ገልጿል፡፡
በተመሳሳይ ዜና ከህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ሰሞኑን ባከናወነው የክትትል እና ቁጥጥር ተግባር 7ሚሊዮን 243 ሺህ 385 የኢትዮጵያ ብር መያዙንም ገልጿል፡፡ ለህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ የተዘጋጁ 117ሺህ 703 የአሜሪካን ዶላር፣400 ዩሮ፣740 የእንግሊዝ ፓውንድ፣700 የደቡብ አፍሪካ ራንድ፣8ሺህ 50 የባበሩት አረብ ኤሚሬትስ ገንዘብ እና የሌሎች የተለያዩ ሃገራት ገንዘቦችን በቁጥጥር ስር ማዋሉንም ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው አብራርተዋል፡፡
በአጠቃላይ ከህገ-ወጥ የገንዘብ ምንዛሬ እና የብር ኖት ቅያሪ ጋር ተያይዞ ከ15 ሚሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ብር በቁጥጥር ስር መዋሉንም ጨምረው ገልፀዋል፡፡ ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር የሚያደርገውን ትብብር አጠናክሮ እንዲቀጥልም ፖሊስ ጥሪ አቅርቧል፡፡