ባሳለፍነው ሳምንት ቅዳሜ ረፋድ የተጀመረው ይህ ጦርነት በሱዳን ሀይልን በበላይነት ለመቆጣጠር በሚል መጀመሩ ተገልጿል
በሱዳን የተኩስ አቁም ቢታወጅም ጦርነቱ ለስምንተኛ ቀን ቀጥሏል።
በጎረቤት ሀገር ሱዳን ከስምንት ቀን በፊት ቅዳሜ ረፋድ ላይ በሱዳን መከላከያ ሰራዊት እና በፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ መካከል የተጀመረው ጦርነት ዛሬም ቀጥሏል።
በጀነራል አብዱል ፋታህ አልቡርሃን እና ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ዳጋሎ ወይም ሄመቲ በሚመሯቸው ወታደሮች መካከል የተጀመረው ይህ ጦርነት ሱዳንን ወደ ከፋ ሁኔታ ወስዷታል።
በጦርነቱ እስካሁን የሞቱ ዜጎች ቁጥር 413 እንደደረሰ የዓለም ጤና ድርጅት ሪፖርት ያስረዳል።
ሁለቱ ተፋላሚ ወገኖች በትናንትናው እለት የተከበረውን የኢድ አልፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ለሶስት ቀናት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ተኩሱ ዛሬም እንደቀጠለ ይገኛል።
በተኩስ አቁሙ መሰረት ለተወሰኑ ቀናት ጦርነት ይቆማል ብለው ተስፋ አድርገው የነበሩ ሱዳናዊያን ጦርነቱ መቀጠሉን ተከትሎ ከመኖሪያ ቤታቸው በመሸሽ ላይ ናቸው ተብሏል።
ተፋላሚ ወገኖቹ ከዚህ በፊትም የ24 ሰዓታት የተኩስ አቁም ስምምነት ለማድረግ ተስማምተው የነበረ ቢሆንም ስምምነቱን መጣሳቸው ይታወሳል።
የትናንቱን የተኩስ አቁም ስምምነትን ተከትሎ በርካታ ሀገራት ዜጊቻቸውን ከካርቱም ለማስወጣት አቅደው የነበረ ቢሆንም ሳይሳካላቸው መቅረቱን በመናገር ላይ ናቸው።
አሜሪካ እስካሁን አንድ ዜጋዋ በሱዳን እንደተገደለባት የገለጸች ሲሆን ሌሎች ዜጎቿን ለማስወጣት ወደ ጅቡቲ ልዩ ኮማንዶዎችን እንደምትልክ ሮይተርስ ዘግቧል።
ጀርመን በበኩሏ በአየር ሀይሏ በኩል ሶስት አውሮፕላኖችን በማሰማራት ከካርቱም ዜጎቿን ለማስወጣት ብትሞክርም ሳይሳካላት መቅረቱን ገልጻለች።
የሱዳን ተፋላሚ ሀይሎች የጀመሩትን ጦርነት እንዲያቆሙ በርካቶች ቢያሳስቡም ወደ ስምምነት መምጣት ያልቻሉ ሲሆን አንዳቸው ሌላኛውን በመክሰስ ላይ እና ለድርድር ፈቃደኛ አለመሆናቸውን በመናገር ላይም ናቸው።