መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስቆም አቅም ሳይሆን ፈቃደኝነት እና ዝግጁነት አጥቷል - አብን
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በጥቃቱ የሸኔ ታጣቂ ቡድንን ተጠያቂ አድርጓል
አብን ጥቃቱን በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችል መዋቅራዊ እና ስርዓት ሰራሽ ሽግግር እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ (አብን) መንግስት በአማራ ህዝብ ላይ የሚደርሰውን ጥቃት ለማስዎም አቅም ሳይሆን ፈቃደኝነት እና ዝግጁነት አጥቷል አለ፡፡
ላለፉት 30 ዓመታት በአማራ ህዝብ ላይ ሲፈጸም የቆየው መዋቅራዊ እና ስርዓታዊ ጥቃት አሁንም በፌዴራል እና በክልል መንግስታት ተገቢው ትኩረት ተነፍጎት እና ሃይ ባይ አጥቶ ተጠናክሮ ቀጥሏል ያለው ንቅናቄው ከሰሞኑ በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን የተፈጸመውን ጥቃት አውግዞ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው ሰኔ 11 ቀን 2014 ዓ.ም በምዕራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ተብሎ በሚጠራ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑ በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሃን አማራዎች ህጻናት እና ሴቶችን ጨምሮ መጨፍጨፋቸውን ገልጿል፡፡
የኦሮሚያ እና የፌዴራሉ መንግስት ባለስልጣናት ጭምር አረጋግጠውታል ካለው ከዚህ ጥቃት ከሞት የተረፉት የአካባቢው አማራዎች አሁንም ድረስ በከፍተኛ ስጋት ውስጥ እንደሚገኙ የተለያዩ መገናኛ ዘዴዎች ዘግበዋል ብሏል፡፡
በአማራ ሕዝብ ላይ በተለያዩ አካባቢዎች ሲፈጸም የኖረው እና እየተፈጸመ ያለውን ጭፍጨፋ እንደተፈጥሯዊ እና መደበኛ ክስተት መወሰዱ የሚያሳዝን ነው ያለው አብን ጥቃቱ የሚፈጽምባቸው የክልሎቹም ሆኑ የፌዴራሉ መንግስታት ጥቃቱን በዘላቂነት ለመከላከልም ሆነ ለማስቆም የሚያስችል ፍላጎትም ሆነ ዝግጁነት እና ፈቃደኛነት እየተስተዋለ አይደለምም ነው ያለው፡፡
በዚህም ጥቃቶቹ በተደራጀ የመከላከል ስራ ሊገቱ የሚችሉ ቢሆንም በሚመለከታቸው አካላት ተገቢው የስጋት ትንተና እና የመከላከል እርምጃ ባለመወሰዱ የንጹሃን ጭፍጨፋ እና ጥቃት ማስቆም እንዳልተቻለም ገልጿል፡፡
መንግስት በሰው ኃይልም ሆነ በማተሪያል ከመቼውም ጊዜ የተሻለ አቅምን ገንብተናል በማለት ተደጋጋሚ መግለጫዎችን በሚያወጣበትና ትዕይንቶችን በሚያከናውንበት በዚህ ወቅት ጭፍጨፋው ተባብሶ መቀጠሉ ጉዳዩ የአቅም ማጣት ሳይሆን የፈቃደኝነት እና የዝግጁነት ማጣት መሆኑን የሚያመላክት ነውም ነው አብን ያለው፡፡
መንግስት አቅም የሌለው ከሆነ፤ ችግሩን አምኖ ሊቀበል እና ለጥቃት ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎችን በማደራጀት፣ በማስታጠቅ እና አመራር በመስጠት ራሳቸውን ሊከላከሉ የሚችሉበትን ሁኔታ ሊፈጥር ይገባ እንደነበርም አስታውቋል፡፡
ጥቃቱ ልዩ ትኩረት የማይሰጥና ጊዜያዊ እና ዘላቂ መፍትሄዎችን የማያገኝ ከሆኑ መዘዙ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን እንደሚተርፍ በማሳሰብም መንግስት ያለምንም ሰበብ ኃላፊነቱን እንዲወጣ እና በራሱ መዋቅር ውስጥ የተሰገሰጉትን ተባባሪዎች ጨምሮ የጭፍጨፋው ተሳታፊዎች ለሕግ እንዲቀርቡ ጠይቋል፡፡
በህይወት ለተረፉና በከፍተኛ ስጋት ውስጥ ለሚገኙት ነዋሪዎች አፋጣኝ የህይወት አድን ድጋፍ፤ ለተጎጅዎችና ለቤተሰቦቻቸውም አስቸኳይ ሰብዓዊ እርዳታ እንዲደረግም ጠይቋል፡፡
ቀጣይ ጥቃቶችን ለመከላከል የሚያስችል በቂ ዝግጅት ይደረግ፤ ነዋሪዎች ራሳቸውን የሚከላከሉበት አስቻይ ሁኔታ ይፈጠር ያለም ሲሆን ጥቃቱን በዘላቂነት ለማስቆም የሚያስችል መዋቅራዊ እና ስርዓት ሰራሽ ሽግግር እንዲደረግ ጥሪ አቅርቧል፡፡
መንግስት የጀመረው የህግ የበላይነትን የማስፈን ስራ በሽብር ቡድኖች ሴራ በፍጹም አይደናቀፍም ሲል መግለዓ ያወጣው የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት በጥቃቱ የሸኔ ታጣቂ ቡድንን ተጠያቂ አድርጓል፡፡
ቡድኑ ህግ በማስከበር ላይ ባሉ የመንግስት የጸጥታ ኃይሎች እየደረሰበት የሚገኘውን ከፍተኛ ሽንፈት ለመሸፈን የጥፋት በትሩን ወደ ንጹሃን ማዞሩንም ነው አገልግሎቱ የገለጸው፡፡
በበቀል የሽብር ተግባሩ በኦሮሚያ ክልል ምእራብ ወለጋ ዞን ጊምቢ ወረዳ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ በርካታ ንጹሃንን ህይወት በግፍ ቀጥፏል፣ ንብረትንም አውድሟል ብሏል በመግለጫው።
ሙሉ በሙሉ እንዲደመሰስ በመላው የክልልና የፌደራል የጸጥታ ሃይሎች የተጀመረው የተቀናጀ ተልዕኮ ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁሟል፡፡