በአጣዬ እና አካባቢው “አስፈላጊውን ጥበቃና ድጋፍ አደርጋለሁ”ያለው መከላከያ ነዋሪዎቹ እንዲመለሱ ጥሪ አቀረበ
ሆኖም ነዋሪዎቹ አሁንም ሊያስተማምን የሚችል ሁኔታ እንደሌለ በመጠቆም ወደ መኖሪያቸው ለመመለስ እንደሚቸግራቸው ገልጸዋል
በአካባቢው የተቋቋመው ኮማንድፖስትም ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ለፍርድ እንደሚያቀርብ አስታውቋል
ወደ አጣዬ ተመልሰው ለመኖር እንደሚቸገሩ ከሰሞኑ በአካባቢው ተቀስቅሶ በነበረው ግጭት ምክንያት የተፈናቀሉ የከተማው ነዋሪዎች ተናገሩ፡፡
ነዋሪዎቹ ወደ ቀያቸው ተመልሶ ለመኖር የሚያስችል አስተማማኝ ሁኔታ አለመኖሩን በስፍራው ጉብኝት ላደረገው የጋዜጠኞች ቡድን ገልጸዋል፡፡
“ተመልሰን እንመጣለን፤ እናጠቃችኋለን፤ ለቃችሁ ውጡ” የሚል ዛቻና ማስፈራሪያ እንደሚደርሳቸውም ነው አንዳንዶቹ የተናገሩት፡፡
ቡድኑ አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎች ከውድመት የተረፉ አንዳንድ ንብረቶቻቸውን ጭነው ከአካባቢው ሲለቁ ተመልክቷል፡፡
በስፍራው የነበረው የአል ዐይን አማርኛ ሪፖርተርም ከአጣዬ በቅርብ ርቀት ላይ ከሚገኘው ካራቆሬ አካባቢ ንብረቶቻቸውን ጭነው የመኖሪያ ቀያቸውን ለቀው የሚወጡ ነዋሪዎችን ተመልክቶ አነጋግሯል፡፡
ሪፖርተሩ “ከቃጠሎ የተረፈ ነው”ያሉትን ንብረታቸውን ሲጭኑ ያገኛቸውና ማንነታቸውን ለመግለጽ ያልፈቀዱ አንድ የካራቆሬ ነዋሪ ለምን ንብረታቸውን እንደሚጭኑ እና ወዴትስ ሊሄዱ እንደሆነ ላቀረበላቸው ጥያቄ “ከማን ጋር ማንንስ አምኜ እዚህ ልቀመጥ” የሚል ምላሽን ሰጥተውታል፡፡
“ወደተገኘበት ወደዘመድ ጋር ለመጠጋት ነው የምሄደው” ያሉም ሲሆን ለመመለስ እንደሚቸግራቸው ገልጸዋል፡፡
ሪፖርተሩ የኮማንድ ፖስቱን፤ የጋዜጠኞችንም ‘መጡ’ መባል ሰምቶ ለጊዜው ተጠልሎ ከነበረበት ከአካባቢው ገጠራማ ስፍራ ወደ አጣዬ ከተማ የመጣ አንድ ተፈናቃይንም አግኝቶ አነጋግሯል፡፡
ግለሰቡ በከተማዋ በሚገኝ አንድ የንግድ ማዕከል ራሱንና ቤተሰቡን የሚያስተዳድርበት የንግድ ሱቅ የነበረው ነው፡፡
ሆኖም “የተረፈ እቃ እንዳለ ለማየት መጣሁ” ያለለት ሱቁ ሙሉ በሙሉ ወድሟል እንደ ግለሰቡ ገለጻ፡፡
እንዲህ ዐይነት እጣ ፋንታ ገጥሟቸው፤ የቤተሰብ አባላቶቻቸውን ጭምር አጥተው በመሃል ሜዳ፣ በሸዋሮቢት እና በሌሎችም የአካባቢው አጎራባች ስፍራዎች የተጠለሉ በርካቶች ናቸው፡፡
በአጣዬ የነበራቸው ሁለት ሆቴል እና መኖሪያ ቤት ሙሉ በሙሉ መውደሙን ተከትሎ ቤተሰባቸውን ይዘው በደብረብርሃን ተከራይተው ለመኖር የተገደዱ አንድ የከተማው ባለሃብት መኖራቸውንም የአል ዐይን ምንጮች አመልክተዋል፡፡
ባለሃብቱ በተመሳሳይ መልኩ ማንነታቸውን ለመግለጽ ባይፈልጉም ባጋጠመው እና እርሳቸው “ወረራ” ሲሉ በገለጹት ችግር ምክንያት ንብረታቸው በሙሉ መውደሙን በመጠቆም “ከአሁን በኋላ ወደዛ ተመልሶ ለመኖርም ሆነ ለመስራት” እንደሚቸግራቸው ተናግረዋል፡፡
በጥቃቱ ዙጢ ከተባለው የሸዋሮቢት ከተማ አስተዳደር አካባቢ ተፈናቅለው በከተማው ወጣቶች ባህልና ስፖርት (ወባስ) አዳራሽ የተጠለሉት ወ/ሮ ዚነት አቡኑም 15 የቤተሰብ አባላቶቻቸውን ይዘው መፈናቀላቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል።
“ከባድ ነው” ባሉት ጥቃት በኃላፊነት ላይ ያሉ የመንግስት አካላት እጅ ጭምር ሳይኖበት እንዳልቀረ መጠርጠራቸውን ተናግረዋል፡፡
“ጥቃቱ ተራ” እንዳይደለ ወደ ስፍራው ላቀኑት ብዙሃን መገናኛዎች የገለጹት የኤፍራታና ግድም እና የቀወት ወረዳ አስተዳዳሪዎችም በጥቃቱ ምክንያት ተበትኖ የሚገኘውን ህዝብ አሰባስቦ ወደ መኖሪያ ቀዬው ለመመለስ እንደሚሰሩ አስታውቀዋል፡፡
“አጋጥሞ የነበረው የጸጥታ ችግር ወደ ሰላምና መረጋጋት ተመልሷል” ያሉት የመከላከያ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ኮሎኔል ጌትነት አዳነ የተፈናቀሉ ወገኖች ወደየቀያቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርበዋል።
“በአሁኑ ወቅት በርካቶች ወደ ቀያቸው እየተመለሱ ነው” ያሉም ሲሆን ሌሎችም እንዲመለሱ ጠይቀዋል።
ዳይሬክተሩ “ወደ ቀያቸው ለሚመለሱ ሁሉ ሰራዊቱ አስፈላጊውን ጥበቃና ድጋፍ”እንደሚያደርግ ማረጋገጣቸውንም ነው ኢዜአ የዘገበው።
በሰውና ንብረት ላይ የደረሰው ጉዳት ተጣርቶ ለሕዝብ ይፋ ይደረጋልም ብለዋል ኮሎኔል ጌትነት።
የጸጥታ ችግሩን ተከትሎ በደቡብ ወሎ፣ ሰሜን ሸዋና የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞኖች በሚገኙ ዘጠኝ ወረዳዎችና አምስት ከተሞች ኮማንድ ፖስት መቋቋሙ የሚታወስ ነው።
ኮማንድ ፖስቱ በተፈፀመው ወንጀል ተጠያቂ የሚሆኑ አካላትን ለፍርድ እንደሚያቀርብ አስታውቋል፡፡
ማህበረሰቡ ተጠርጣሪዎችን እያጋለጠ እንደሆነም ነው የኮማንድ ፖስቱ አስተባባሪ ሌተናል ጄኔራል ደስታ አቢቼ የተናገሩት።