ሩሲያ በመጋዘን ውስጥ የነበረ የዩክሬን ሚሳኤልና የተዋጊ አውሮፕላ ጥይት ማውደሙን አስታወቀች
የዩክሬን ባለስልጣናት፤ በጦርነቱ አራት የሩሲያ ጄነራሎች መገደላቸውን እየተገለጹ ነው
ሞስኮ እና ኪቭ የድል ሽሚያ ውስጥ ገብተዋል እየተባለ ነው
ሩሲያ በዩክሬን በሚገኝ የመሳሪያ ክምችት ላይ ጥቃት መሰንዘሯንና ማውደሟን የመከላከያ መስሪያ ቤቷ አስታወቀ።
ሞስኮ፤ እያደረኩት ነው ባለችው ልዩ ወታደራዊ ተልዕኮ ድል እየተቀዳጀች መሆኗን እየገለጸች ነው። ዩክሬን በበኩሏ አራት የሩሲያ የጦር መሪዎችን ከመግደልም ባለፈ “ድል በድል ሆለሁ” እያለች ነው።
ዛሬ ደግሞ ሩሲያ በመጋዘን ውስጥ ተከማችቶ የነበረ ሚሳኤል እና የተዋጊ አውሮፕላ ጥይት ማውደሟን ይፋ አድርጋለች።
ሞስኮ ይህንን ድል ያገኘችው ኢቫኖ ፍራንኪቭስክ ግዛት መሆኑን ገልጻለች። የሩሲያ ጦር ይህንን ያደረገው ሃይፐርሶኒክ የተሰኘ ሚሳኤል በመጠቀም እንደሆነም መከላከያ መስሪያ ቤቱ ተናግሯል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ትናንትና የክሬሚያን ወደ ሩሲያ መጠቃለል አስመልክቶ በስታዲዬም ውስጥ በተዘጋጀ ስነ ስርዓት ላይ ንግግር ቢያደርጉም ስለዩክሬን አላነሱም ተብሏል።
የዩክሬን እና የሩሲያ ጦርነት ከተጀመረ አራት ሳምንታት ተቆጥረዋል፡፡ በዚህ ጦርነት ውስጥ ዩክሬናውያን እና ፕሬዝዳንታቸው ቮሎድሚር ዘለንስኪ ሀገራቸውን ለመጠበቅ ስርተውታል በተባለ ስራ ለኖቤል የሰላም ሽልማት እንዲታጩ የአውሮፓ ፖለቲከኞች ጠይቀዋል።
ሩሲያ በዩክሬን በወታደራዊ ተቋማት ላይ ጥቃት መሰንዘሯንና ድል ማግኘቷን እየገለጸች ሲሆን ዩክሬንም በተመሳሳይ ድል ላይ እንደሆነች እያስታወቀች ነው።
የሞስኮ እና ኪቭ ፖለቲከኞች በጠብመንጃም በጠረንጴዛም እየተፋለሙ ሲሆን ሰላም የራቃቸው ዜጎች ግን አሁን ዩክሬንን ለቀው መውጣት ጀምረዋል።