ዩክሬን፤ ተዋጊዎቿ እጅ እንዲሰጡ በሩሲያ የቀረበላትን ጥያቄ ውድቅ አደረገች
ሩሲያ በማውሪፖል ከተማ የመሸጉ የዩክሬን ተዋጊዎቿ እጅ እንዲሰጡ አሳስባ ነበረ
ዩክሬን የሚሰጥ ከተማም ሆነ የሚወርድ ጦር የለም ስትል ለሩሲያ ምላሽ ሰጥታለች
ዩክሬን በማውሪፖል ከተማ የመሸጉ ተዋጊዎቿ እጅ እንዲሰጡ በሩሲያ የቀረበላትን ጥያቄ ውድቅ አደረገች፡፡
የወደብ ከተማዋን መክበቧን ያስታወቀችው ሩሲያ ዛሬ ሰኞ ከረፋድ ጀምሮ ሰብዓዊ አቅርቦትን እንደምትፈቅድ በማስታወቅ በከተማ የሚገኙ ዩክሬናውያን ጦር እንዲያወርዱና እንዲወጡ ጠይቃ ነበር፡፡
የኪቭ ባለስልጣናት ለዚህ የጽሁፍ ማረጋገጫ እንዲሰጧትም ነበር ሞስኮ የጠየቀችው፡፡ ሆኖም የዩክሬን ባለስልጣናት ጥያቄውን ውድቅ አድርገዋል፡፡
የሚሰጥ ከተማም ሆነ የሚወርድ ጦር እንደሌለም ነው ባለስልጣናቱ ያስታወቁት፡፡ ሆኖም ወደ ከተማዋ የሚያስገቡ ሰብዓዊ ኮሪደሮች እንዲከፈቱ እንፈልጋለን ብለዋል፡፡
ከጥያቄው ጋር በተያያዘ ምላሽ የሰጡት ዬክሬን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ኢሪና ቨርስቹክ ለሩሲያ ባለስልጣናት “ስምንት ገጽ ደብዳቤ በመጻፍ ጊዜያችሁን ከምታባክኑ ኮሪደሩን ክፈቱ” የሚል ምላሽ መስጠታቸውን ተናግረዋል፡፡
ማውሪፖል በጠቃሚ ስትራቴጂካዊ ስፍራነታቸው ከሚጠቀሱ የዩክሬን ከተሞች መካከል አንዷ ነች፡፡ ወደ ጥቁር ባህር የሚያቋርጠው የአዞቭ ባህር መተላለፊያም በዚህችው ከተማ አቅራቢያ የሚገኝ ነው፡፡ ሆኖም ሩሲያ የአዞቭ ባህር መተላለፊያን በቆረጣ ይዛለች፡፡ ይህም ደቡባዊ ዩክሬንን በቀላሉ ለመቆጣጠር የሚያስችላት ነው፡፡
ከተማዋን ለመቆጣጠርም ትናንትን ጨምሮ ከሰሞኑ ከባድ ውጊያዎች ሲደረጉ ነበረ፡፡ በውጊያዎቹ ታዋቂ ብረት አምራች ተቋማትን ጨምሮ በከተማዋ የሚገኝ ታዋቂ የኪነ ጥበብ ማስተማሪያ ትምህርት ቤት እንዲሁም የገበያ ስፍራዎች መውደማቸው ሲነገር ነበረ፡፡
ሩሲያ ትናንት ‘ኪንዣል’ የተሰኘና ከድምጽ በ10 እጥፍ የሚፈጥን ‘ሃይፐርሶኒክ’ ሚሳዔል ለመጀመሪያ ጊዜ በጦርነቱ መጠቀሟን አስታውቃ ነበረ፡፡ ሚሳዔሉ በደቡባዊ ዩክሬን የሚገኙ የሃገሪቱ ጦር የነዳጅ ዴፖዎችን ዒላማ ያደረገ ነበር ተብሏል፡፡ ሆኖም ዩክሬን ሚሳዔሉ ንጹሃንን ዒላማ ያደረገ ነው የሚል ክስ አቅርባለች፡፡