አሁን ያለው ጦርነት ለሩሲያ “የሕልም ቅዠት” እንደሆነባት ዩክሬን ገልጻለች
ከሩሲያ ጋር ውጊያ ውስጥ ያሉት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዘለንስኪ የሩሲያ ወታደሮች እጃቸውን እንዲሰጡ ጥሪ አቀረቡ።
የሩሲያ ወታደሮች እጃቸውን ለዩክሬን ጦር ከሰጡ የመኖር ዕድል እንዳላቸው ፕሬዝዳንቱ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል። ወታደሮቹ የመኖር ዕድሉን የሚያገኙት መሳሪያቸውን አስቀምጠው እጃቸውን ለዩክሬን ጦር ለመስጠት ከወሰኑ ብቻ እንደሆነ ጠቅሰዋል።
የሩሲያ ወታደሮች ይህንን ካደረጉ ዩክሬን አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግምገልጸዋል።
“እጃችሁን ከሰጣችሁ እንክብካቤና በህይወት የመኖር ዕድል እንደምታገኙ በዩክሬን ሕዝብ ስም እነግራኋለሁ” ሲሉም ነው ዘለንስኪ ያስታወቁት።
የሩሲያ ወታደሮች እጃቸውን ለዩክሬን ጦር ከሰጡ የሰው ልጅ የሚያስፈልገው እንክብካቤ እንደሚደረግላቸውም የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቃል ገብተዋል።
እጃቸውን ለዩክሬን የሚሰጡ የሩሲያ ወታደሮች የሚደረግላቸው እንክብካቤ የሩሲያ ጦር የዩክሬንን ሕዝብ እየያዘበት ካለው መንገድ የተለየ እንደሆነም ፕሬዝዳንቱ ገልጸዋል። አሁን ያለው ጦርነት ለሩሲያ “የሕልም ቅዠት” እንደሆነባትም ፕሬዝዳንቱ ተናግረዋል።
ዘለንስኪ ምንም እንኳን የሩሲያ ወታደሮች እጅ እንዲሰጡ ጥሪ ቢያደርጉም ከሩሲያ ጋር ያለው ንግግር ዛሬ እንደሚቀጥል ተናግረዋል።
የዩክሬኑ ፕሬዝዳንትና ሌሎች ባለስልጣናት ከሩሲያ ጥቃት እንዲታደጓቸው አሜሪካን፣ አውሮፓንና የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ)ን በተደጋጋሚ እየተማጸኑ ነው።