ደስተኛ ለመሆን የሚያግዙ አምስት ልማዶች
በአመት 700 ሺህ ሰዎች ራሳቸውን እንዲያጠፉ ድብርት፣ ተስፋ መቁረጥ፣ ሀዘን እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ቀዳሚ ምክንያት ናቸው
በአለም አቀፍ ደረጃ 40 በመቶ የሚሆኑ በአዋቂ እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ደስተኛ እንዳልሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ
ደስተኛ ለመሆን የሚያግዙ አምስት ልማዶች
በአለም አቀፍ ደረጃ 40 በመቶ የሚሆኑ በአዋቂ እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች ደስተኛ እንዳልሆኑ መረጃዎች ያሳያሉ
በርካታ ውጥረት እና ውጥንቅጥ በሞላባት አለም ውስጥ ሰዎች መሰረታዊ የኑሮ ጥያቄን ለመሙላት ከሚያደርጉት ግብግብ ባለፈ ደስተኛነትን ፍለጋ በርካታ ጊዜያቸውን ያጠፋሉ፡፡
ደስተኛ የመሆን ሚስጥር በተለያዩ ምሁራን እና ፈላስፎች የተለያየ ትርጓሜ ቢሰጠውም ሰዎች እንደሚገኙበት ኢኮኖሚያዊ ፣ የጤና እና ማህበራዊ ሁኔታ ደስተኝነትን የሚለኩበት መንገድ ይለያያል፡፡
በድብርት ተስፋ በመቁረጥ ፣ የህይወት ትርጉም በማጣት ፣ በጭንቀት ፣ ሀዘን እና በኢኮኖሚያዊ ሁኔታዎች በአመት 700 ሺህ ሰዎች እራሳቸውን ያጠፋሉ፡፡
በተለያዩ ጊዜ የተደረጉ ጥናቶች ደግሞ በአለም አቀፍ ደረጃ 40 በመቶ በአዋቂ እድሜ ላይ የሚገኙ ሰዎች በሕይወታቸው ደስተኛ ስላለመሆናቸው መናገራቸውን ይጠቁማሉ፡፡
ደስተኛ የመሆን ሚስጥር እንደ ሰው እና አካባቢው ቢለያይም የስነልቦና ሀኪሞች ማንኛውም ሰው በቀላሉ ተግብሯቸው ደስተኛ ሊሆንባቸው የሚችሉ በሚል የዘረዘሯቸውን አምስት ልማዶች እንመልከት፡፡
1. ለሰዎች ደግ መሆን ወይም በጎ ማድረግ
ሰዎች ካላቸው ነገር ላይ ቀንሰው ለሰዎች በጎ ነገርን ማድረግ ደስታ ከሚፈጥሩ የመኖር ትርጉም ጥያቄን ከሚመልሱ ልማዶች መካከል አንዱ ነው ተብሏል፡፡
ከመልካምነት በመነጨ ስሜት ለሌሎች ሰዎች የሚደረግ መልካምነት ሰዎች ስለሚገኙበት ሁኔታ አመስጋኝ እንዲሆኑ ፣ በራሳቸው እንዲተማመኑ እና ስለራሳቸው መልካም ስሜት እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡
በዚህ ምግባር ምክንያት በማህበረሰብ ውስጥ እና በሚገኙበት አካባቢ ሰዎች የሚሰጧቸው አክብሮት እና ተቀባይነት ስለሚጨምር በሰዎች ዘንድ መወደዳቸው ደስታን ይፈጥራል ተብሏል፡፡
ትንሽ የሚባል የደግነት ምግባር የለም የሚሉት የስነልቦና ተመራማሪዎቹ ሰዎች አካባቢያቸውን በደንብ ቢቃኙ መልካም ለመሆን ገንዘብ ማውጣት የማይጠይቁ ምግባሮችን ያገኛሉ ብለዋል፡፡
2. አመስጋኝነት
ምስጋና በሀይማኖታዊው ትእዛዛትም በጎ ምግባር ተደርጎ የሚወሰድ ነው። ስለተሰጣቸው ነገር የሚያመሰግኑ ሰዎች ስለጎደላቸው ስለማይጨነቁ እንዲሁም በቁሳቁሳዊ ጉዳዮች ራሳቸውን ለማነጻጸር ጊዜ ስለማይኖራቸው ደስተኞች መሆን እንደሚችሉ ተገልጿል፡፡
ሰዎች ወደ መኝታቸው ከማቅናታቸው በፊት አልያም ከቅርብ ሰዎቻቸው ጋር ሲወያዩ አመስጋኝ ስለሆኑባቸው ፣ በሕይወታቸው ስለተሰጧቸው ነገሮች ማመስገንን ልማድ ማድረግ አለባቸው ተብሏል፡፡
ለምሳሌ በነጻነት መንቀሳቀሳቸው ፣ በህመም አልጋ ላይ ባለመዋላቸው ፣ ሙሉ አካል እና ሙሉ ጤና ስላለቸው እንዲሁም ለሌሎች ውድ የሆኑ እነርሱ ጋር ግን ያሉ ነገሮችን በመቁጠር አመስጋኝ እንዲሆኑ ይመከራል፡፡
3. መልካም ግንኙነትን ከሰዎች ጋር መመስረት
ማህበራዊ እንስሳ እንደሆነ የሚነገርለት የሰው ልጅ በምድር ላይ ብቸኛ ይሆን ዘንድ መልካም አይደለም፡፡
ከቤተሰብ ፣ ከልጆች ፣ ከጎረቤት ፣ ከጓደኛ በአካባቢ ከሚገኙ ሰዎች ጋር ግንኙነትን የተቃና ማድረግ የደስተኛነት ሚስጥር ከሆኑ ልማዶች መካከል አንዱ ተደርጎ ተጠቅሷል፡፡
ሰዎች ከሌሎች ጋር የሚኖራቸው መስተጋብር አካባቢያቸው ከጭንቀት እና ድብርት እንዲሁም ያለመፈለግ ስሜትን ስለሚያጠፋ ለመኖር ተጨማሪ ምክንያትን የሚያክል ነው ሲሉ የስነ ልቦና ተመራማሪዎቹ ተናግረዋል፡፡
በችግር እና ደስታ ጊዜ በአቅራቢያ የሚገኝ ሰው መኖር እንዲሁም በወዳጆች መከበብ ሰዎች ደህንነት እና በራስ መተማመን እንዲሰማቸው ያደርጋል፡፡
4. መልካም ዜናዎችን በተገቢው መጠን ማጣጣም
በርካታ የጭንቀት እና የሀዘን ዜናዎች በሞሏት አለም ውስጥ መልካም ዜናዎች ከብዙ ጊዜ አንድ ጊዜ የሚገኙ በመሆናቸው በልካቸው መከበር ይገባቸዋል፡፡
በህይወት ውስጥ የሚያጋጥሙ መልካም አጋጣሚዎችን እና የስኬት ወሬዎችን ከቅርብ ሰዎች ጋር በመሰባሰብ ማክበር ህይወት አንድ አይነት እና አሰልቺ እንዳትሆን ከማገዙም በላይ በተሰፍ የተሞላ ነገ እንዲኖር ያደርጋል፡፡
በዚህም በስራ እና በህይወት ስላጋጠሙን ስኬቶች ደስታን በተገቢው መንገድ መግለጽ ይመከራል፡፡
5. ከሰዎች አለመጠበቅ
ለሰዎች ስኬት እና ውድቀት ቀዳሚ ሃላፊነቱን የሚወስዱት ራሳቸው ናቸው፡፡
መልካም ወዳጅነትን መመስረት ለደስተኛነት ወሳኝ ቢሆንም ደስተኛነት በሰዎች ላይ መንጠልጠል አይኖርበትም፡፡
ለሰዎች በሰጠናቸው መጠን ምላሽ የምንጠብቅ ከሆነ የታሰበው ሳይሆን ሲቀር ደስተኛ አለመሆንን እና ስለራስ መጥፎ ስሜት እንዲሰማ በማድረግ ከሰዎች መራቅን እና ብቸኝነትን ያስከትላል፡፡
በመሆነም ደስተኛ ለመሆን የሚፈልጉ ሰዎች የደስተኘነት ምክንያታቸው በሰዎች ላይ መመርኮዝ የለበትም ብለዋል የሰነ ልቦና ሀኪሞቹ።