ከባህር ስር 1 ሺህ ሜትር ጥልቀት ላይ የሚጓዘው ድሮኑ፤ እስከ 10 ሺህ ኪ.ሜ ድረስ መሸፈን ይችላል
ሩሲያ በያዝነው የፈረንጆቹ 2022 ይፋ ካደረገቻቸው አውዳሚ የጦር መሳሪያዎች ውስጥ “ፖሲዶን” የባህር ሰርጓጅ ድሮን አንዱ ነው።
“ፖሲዶን” ሰርጓጅ ድሮን የምጽአት ቀን የሚል መጠሪያ በተሰጠው የሩሲያው ቤልግሮድ ሰርጓጅ መርከብ ላይ የሚገጠሙ ሲሆን፤ ከሰርጓጅ መርከቡ ላይ የሚወነጨፉ መሆኑም ታውቋል።
“ፖሲዶን” የሩሲያ ኒውክሌር ድሮን ምን የተለየ ያደርገዋል?
“ፖሲዶን” በባህር ስር የሚጓዝ ድሮን ሲሆን፤ የኒውክሌር አረር የሚሸከም ግዙፍ የሆነ የባህር ሰርጓጅ ድሮን ነው።
የውሃ ስር ድሮን ፕሮጀክቱ መሰራት እንደተጀመረ የሚያሳየው መረጃ በ2015 ላይ እንደወጣ የዘገበው ኢውሮ ኒውስ፤ የድሮኑ ዋነኛ ዓላማም የባህር ዳርቻ ላይ የሚገኙ የጠላትን ወታራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ስፍራዎችን ለማውደም ነው።
“ፖሲዶን” የኒውክሌር የባህር ሰርጓጅ ድሮን 20 ሜትር ርዝመት ያለው ሲሆን፤ ከባህር ስር እስከ 1000 ሜትር ጠልቆ መጓዝ እንደሚችልም ተመላክቷል።
የባህር ስር ድሮኑ እስከ 10 ሺህ ኪሎ ሜትር ድረስ የማካለል እና የጠላትን ኢላማ የመምታት አቅም ያለመው መሆኑም ተመላክቷል።
አብዛኛው የባህር ስር ድሮኑ ዝርዝር መረጃዎች እስካሁን በሚስጥር የተያዙ ሲሆን፤ ካለው ፍጥነት የተነሳ መከላከልም ሆነ ለማስቆም አዳጋች እንደሆነ ግን ተነግሯል።
የባህር ስር ድሮኑ ሰው ሰራሽ ሱናሚ ማእበሎችን ማስነሳት ይችላል የተባለ ሲሆን፤ እስከ 500 ሜትር ርዝመት ያለው ሱናሚ በማስነሳትም የባህር ዳርቻ ከተሞችን እንዳልነበሩ አድርጎ ሙሉ በሙሉ ማውደም ይችላል ተብሏል።
የብሪታኒያው ዴይሊ ሜይል ጋዜጣ እንዳስነበበው እነዚህን ድሮኖች የተሸከመው ቤልግሮድ ሰርጓጅ መርከብ ባሳለፍነው ሰኔ ወር ላይ በነጭ ባህር ላይ መታየቱን እና በወቅቱም ዲሚትሪ ዶንስኮይ የተባለ ሌላ የጦር መርከብ አብሮት እንደበረ ይታወሳል።