ለዩክሬን የረጅም ርቀት መሳሪያ ማስታጠቅ ቀይ መስመርን ማለፍ ነው ስትል ሩሲያ አስጠነቀቀች
ዩክሬን የረጅም ርቀት ተተኳሽ የጦር መሳሪያ እንዲሰጣት ለአሜሪካ ጥያቄ አቅርባለች
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 206ኛ ቀኑ ላይ ይገኛል
ለዩክሬን የረጅም ርቀት መሳሪያ ማስታጠቅ ቀይ መስመርን ነው ስትል ሩሲያ አስጠነቀቀች፡፡
ከስድስት ወር በፊት የተጀመረው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት አሁንም እንደቀጠለ ሲሆን ሀያላን ሀገራት ጎራ ለይተው ድጋፍ በማሰባሰብ ላይ ይገኛሉ፡፡
በዚህ ጦርነት ሩሲያ እንድትሸነፍ አሜሪካ እና የአውሮፓ ሀገራት ለዩክሬን የተለያዩ ዘመናዊ የጦር መሳሪያዎችን በማስታጠቅ ላይ ናቸው፡፡
ዩክሬንም ከነዚህ ሀገራት የሚደረግላትን የጦር መሳሪያ በመጠቀም በሩሲያ ተይዘው የነበሩ ቦታዎችን መልሳ በማስለቀቅ ላይ ስትሆን አሜሪካ የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ የጦር መሳሪያዎች እንዲሰጧት ጠይቃለች፡፡
ሩሲያ በበኩሏ ለዩክሬን የረጅም ርቀት ተምዘግዛጊ የጦር መሳሪያ ማስታጠቅ ማለት ቀይ መስመርን ማለፍ ነው ስትል አስጠንቅቃለች፡፡
የሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ እንዳሉት አሜሪካ ለዩክሬን የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያ ካስታጠቀች ሞስኮ ራሷን ለመከላከል ስትል እርምጃ ትወስዳለች ማለታቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የአሜሪካ መከላከያ ዋና አዛዥ ሊዮድ ኦስቲን ሀገራቸው ለዩክሬን ተጨማሪ የ675 ሚሊዮን ዶላር ግምት ያላቸው የጦር መሳሪያዎች ልትሰጥ እንደምትችል ተናግረዋል፡፡
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በበኩላቸው ከአሜሪካ እና ምዕራባዊያን በሚደረግላቸው የጦር መሳሪያ ድጋፍ በሩሲያ ጦር ተይዘው የነበሩ አካባቢዎችን እያስለቀቁ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሩሲያ የተያዙ ሌሎች የዩክሬን ግዛቶችን ለማስለቀቅም የረጅም ርቀት የጦር መሳሪያዎች እና ሌሎች አጋዥ መሳሪያዎች ድጋፍ እንዲደረግላቸው ለአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት ሀገራት ጥያቄ አቅርበዋል፡፡
ለሰባት ወራት በዘለቀው የሩሲያ ጦርነት ከሁለቱም ወገኖች በርካታ ወታደሮች እና ንጹሃን የተገደሉ ሲሆን ከ10 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ደግሞ ወደ ጎረቤት ሀገራት እንደተሰደዱ ተመድ ገልጿል፡፡