የዩክሬኖቹ ሉሃንስክ እና ዶንቴስክ ግዛቶች ወደ ሩሲያ ለመቀላቀል ህዝበ ውሳኔ ሊያደርጉ ነው
ሁለቱ ግዛቶች ከሶስት ቀናት በኋላ ለህዝበ ውሳኔ ድምጽ ይሰጣሉ ተብሏል
ዩክሬን ከዚህ በፊት ህዝበ ውሳኔውን መቃወሟ ይታወሳል
የዩክሬኖቹ ሉሃንስክ እና ዶንቴስክ ግዛቶች ወደ ሩሲያ ለመቀላቀል ህዝበ ውሳኔ ሊያደርጉ ነው፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ወይም ኔቶን እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ነበር የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት የተጀመረው፡፡
በዚህ ጦርነት በርካታ ጉዳት ያደረሰ ሲሆን የሩሲያ ጦር ወደ ዩክሬን ዘልቆ በመግባት ሉሃንስክ እና ዶንቴስክን ጨምሮ አራት ግዛቶችን ተቆጣጥሯል፡፡
ከሩሲያ ጋር የሚዋሰኑት የዩክሬን ግዛቶች የሆኑት ሉሃንስክ እና ዶንቴስክ ግዛቶች በህዝበ ውሳኔ ወደ ሩሲያ ለመቀላቀል ከፈረንጆች መስከረም 23 እስከ 27 ድረስ ፕሮግራም መያዛቸውን ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዚህ በፊት ለሁሉም የዩክሬን ዜጎች የሩሲያ ፓስፖርት እንዲሰጣቸው የሚያስችል አዋጅ ማውጣታቸው ይታወሳል።
ሞስኮ ከዚህ በፊት በሩሲያ ቁጥጥር ስር በዋሉ የዩክሬን ከተሞች ውስጥ የሚኖሩ ዜጎች ፓስፖርት ስትሰጥ የቆየች ሲሆን፤ በመቀጠልም ለሁሉም የዩክሬን ዜጎች የሩሲያ ፓስፖርት እንዲሰጣቸው የፕሬዝዳንት ፑቲን መንግስት አውጇል ተብሏል፡፡
ዩክሬን በበኩሏ “ሩሲያ እያደረገችው ያለው ተግባር በግዛቴ ውስጥ የሩሲያ ዜጎች መፍጠር ነው” በማለት ማውገዟ ተገልጿል።
ሩሲያ በዩክሬን ግዛት ውስጥ ፓስፖርት መስጠት መጀመሯ የዩክሬንን የግዛት እንድነት የሚፈታተን እና ዓለም አቀፍ ህጎችን የጣሰ መሆኑንም አስታውቃለች።
በቅርቡም የመጀመሪያው የሩሲያ ባንክ በሩብል መገበያየትና የሩሲያን የቴሌኮምና ሌሎችንም አገልግሎቶች መጠቀም በጀመረው የኬርሶን አካባቢ በቅርቡ ስራ እንደሚጀምር የአካባቢው የአስተዳደር አካላት ማስታወቃቸው ይታወሳል።
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ከዚህ በፊት በሰጡት መግለጫ የዘመናዊቷ ሩሲያ ዕጣ ፋንታ የሚወሰነው የቀድሞ ግዛቶቿን ማስመለስና ማጠናከር መሆኑን ማስታወቃቸውም አይዘነጋም፡፡