ሩሲያን ለቀው የወጡ የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች 107 ቢሊዮን ዶላር መክሰራቸው ተገለጸ
በሩሲያ የተሰማሩ የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች አሁንም 223 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ ሀብት አላቸው ተብሏል
የአውሮፓ ህብረት እና ሩሲያ አንዳቸው የሌላውን ሀብት ለመውረስ መንገዶችን እያፈላለጉ እንደሆኑ ተገልጿል
ሩሲያን ለቀው የወጡ የውጭ ሀገራት ኩባንያዎች 107 ቢሊዮን ዶላር መክሰራቸው ተገለጸ፡፡
ሩሲያ ለልዩ ዘመቻ በሚል ለአንድ ሳምንት ያህል የሚቆይ ዘመቻ ለማድረግ ጦሯን ወደ ዩክሬን በመላክ የተጀመረው ጦርነት ከተጀመረ ሶስተኛ ዓመቱን ይዟል፡፡
ይህን ጦርነት ተከትሎም ሩሲያ ጦርነቱን እንድታቆም ከአውሮፓ ህብረት እና ኔቶ አባላት ከ10 ሺህ በላይ ማዕቀቦች ተጥሎባታል፡፡
በዚህ ምክንያት በሩሲያ ተሰማርተው የነበሩ የተለያዩ የዓለማችን ሀገራት የኢንቨስትመንት ኩባንያዎች ሞስኮን እየለቀቁ ለመሰደድ የተገደዱ ሲሆን እነዚህ ኩባንያዎች በ2022 ዓመት ብቻ 107 ቢሊዮን ዶላር ኪሳራ አስመዝግበዋል ሲል ሮይተርስ ዘግቧል፡፡
እንደዘገባው ከሆነ ድርጅቶቹ በሩሲያ የነበራቸውን ስራ እየሸጡ የወጡ ሲሆን ሩሲያም እነዚህ ተቋማት ሀብታቸውን በቅናሽ እየሸጡ እንዲወጡ ታበረታታለች የተባለ ሲሆን መስራት እና መቆየት የሚፈልጉትን ግን ጫና እንደማታደርግ ተገልጿል፡፡
ይሁንና መሰረታቸውን በሩሲያ ላይ ማዕቀብ የጣሉ ሀገራት ውስጥ ያደረጉ ኩባንያዎች ላይ ግን ጥብቅ ክትትል እንደምታደርግባቸው፣ ለቀው መውጣት ቢፈልጉም በቢሮ ክራሲ እየተንገላቱ ነውም ተብሏል፡፡
ሩሲያ ከዩክሬን ባሻገር በሌሎች ሀገራት ጦርነት ለመክፈት አስባለች?
በዩክሬን ጦርነት ምክንያት አውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ 300 ቢሊዮን ዶላር ዋጋ ያለው የሩሲያ ሀብትን ያገዱ ሲሆን ለዩክሬን ጉዳት ካሳ ሊያውሉት እንደሚችሉ በተደጋጋሚ ተናግረዋል፡፡
ሩሲያም የአጸፋ እርምጃ እንደምትውስድ ያስጠነቀቀች ሲሆን በተለይም 223 ቢሊዮን ዶላር የሚያወጣ የምዕራባዊያን ሀገራት ኩባንያዎች ሀብትን እንደምትወርስ ገልጻለች፡፡
የጀርመን፣ ብሪታንያ፣ አሜሪካ፣ ፈረንሳይ እና ሌሎችም ሀገራት ኩባንያዎች አሁንም በሩሲያ ገበያ ውስጥ እየሰሩ እንደሆነ በዘገባው ላይ ተጠቅሷል፡፡