በኢትዮጵያ “አሁን ያለው ወቅት ከ1969 ዓ.ም ጋር ይመሳሰላል”-የቀድሞ የኢትዮጵያ ባለስልጣን
መንግስትን እና አማጺ ኃይልን እኩል ከሚያደርጉ አካላት ጋር መነጋገር እንደማይገባ ገልጸዋል
ኢትዮጵያ ወደ ምስራቅ ጎራ ብታዘነብል የሚፈረድባት ሊሆን አይችልም ሲሉ ባለስልጣኑ ተናግረዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በፕሬዝዳንት ረሲፕ ጣኢብ ኤርዶሃን ግብዣ ከትናንት በስቲያ ወደ አንካራ በመሄድ ከፕሬዝደንቱ ጋር በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፈው እሁድ ዕለት በማህበራዊ ትስስር ገጾቻቸው ባወጡት መግለጫ ፤የምዕራቡ ዓለም ዲፕሎማሲ እና ሚዲያ፤ የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ እና የህወሃትን ድምጽ “በማስተጋባት“ ደጀን በመሆን ጥረቱን እንደቀጠለ ገልጸዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያውያን ተረባርበው የሚደረገውን ጫናውን እንዲቋቋሙ ጥሪ አድርገዋል፡፡
በኢትዮጵያ ወቅታዊ ፖለቲካ እና የውጭ ግንኙነት ዙሪያ፤ በደርግ ዘመነ መንግስት የማስታወቂያ ኮሚቴ አባል፤ የወታደራዊ ፖለቲካ ጠቅላይ ፕሮፖጋንዳ ኃላፊ ከነበሩት እና “ነበር” የሚለውን ጨምሮ በርካታ መጽሐፍትን ከደረሱት ገስጥ ተጫኔ ጋር አል ዐይን አማርኛ ቆይታ አድርጓል፡፡
አቶ ገስጥ፤ ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ጊዜ ብዙ ወዳጅ እንደማይኖራት ገልጸው ለዚህም አብነት የሚሆኑት ሁለተኛው የዓለም ጦርነት እና የሶማሊያ ወረራን እንደሆኑ አንስተዋል፡፡ አሁን ኢትዮጵያ ያለችበት ወቅት በ1969 ዓ.ም ከገጠማት ጋር እንደሚመሳሰል ያነሱት አቶ ገስጥ በወቅቱ ኢትዮጵያ የተዳከመች የመሰላቸው ሀገራት ከጎኗ ከመሆን ይልቅ ጥቃት መሰንዘር ላይ ያተኩሩ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ሱዳን በ1969 ዓ.ም ኢትዮጵያ ችግር በገጠማት ጊዜ ጥቃት ሰንዝራ እንደነበር እና እንደተሸነፈች ያስታወሱት ገስጥ “የአሁኑ ሁኔታም ከያኔው ጋር እንደሚመሳሰል” ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
በ 1969 ዓ.ም አሜሪካ ከፍተኛ የመሳሪያ ማዕቀብ አድርጋ እንደነበር የገለጹት አቶ ገስጥ አሁን ላይም አጋሮቿን በማሰባሰብ ኢትዮጵያ ላይ እያዘመተች እንደሆነም ያነሳሉ፡፡ ምዕራባውያን ያኔም አሁንም ጣልቃ ገብነትን እንደሚያንጸባርቁ የሚገልጹት የቀድሞው የኢትዮጵያ ባለስልጣን፤ አሁን ያለው ጣልቃ ገብነት ግን በሌሎች ጊዜያት ካለው በበለጠ በከፍተኛ የፕሮጋንዳ ዘመቻ የታገዛ ነው ብለዋል፡፡
አቶ ገስጥ፤ የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የቱርክ ጉብኝት ኢትዮጵያ ካለባት ችግር እና ከምዕራባውያን “ርብርብ” አኳያ አማራጭ መንገድ መፈለጉ “እጅግ በጣም“ አስፈላጊ እንደሆነ ገልጸው ወደ ቱርክም፣ሩሲያም እንዲሁም ወደ ቻይናም እንዲሁም አሁን ኢትዮጵያ ያለችበትን ሁኔታ ከሚደግፉ ኃይሎች ጋር ሆኖ መስራት“ የግድ አስፈላጊ ነው“ ይላሉ፡፡ የአሁኑ የቱርክ ጉብኝትም ከዚህ ጋር የተያያዘ እንደሚሆን እንደሚገምት ያነሱት አቶ ገስጥ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ቱርክ መጓዛቸው ትክክል መሆኑን ተናግረዋል፡፡
“በአንድ ሀገር ሁለት መንግስት ሊኖር አይገባም“ የሚሉት የቀድሞው የመንግስት የሥራ ኃላፊ አሁን መንግስት በህወሃት ላይ የጀመረው የህልውና ዘመቻ መጠናቀቅ እንዳለበት እና ሕዝቡም ከመንግስት ጎን ሊቆም ይገባል ይላሉ፡፡
የአሜሪካ መንግስት ወደ ኢትዮጵያ የላካቸው የአሜሪካ ተራዲኦ ድርጅት (ዩኤስ አይድ) ዋና ዳይሬክተር ሳማንታ ፓወር እና የአሜሪካ የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ጄፍሪ ፌልትማን ወደ ኢትዮጵያ የመጡ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሁለቱንም የሥራ ኃላፊዎች አለማግኘታቸው ትክክለኛ ውሳኔ እንደሆነ አቶ ገስጥ ተናግረዋል፡፡
“ኢትዮጵያን በየትኛውም መድረክ፤ በየትኛውም ቦታ ላይ ለማዋረድ የሚፈልጉ ኃይሎችን እንዴት ማነጋገር ይቻላል?“ ሲሉም አቶ ገስጥ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ መንግስትን እና አማጺ ኃይልን እኩል የሚያደርጉ ወይንም ሀገርን “ችግር ማጥ ውስጥ“ ከሚያስገባ ኃይል ጋር ተደራደሩ ማለት አስቸጋሪ እንደሆነ የገለፁት አቶ ገስጥ ጠቅላይ ሚኒሰትሩ ሁለቱንም የአሜሪካ ባለስልጣን አለማነጋገራቸው ተመራጭ ነው ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ በትግራይ ክልል ጥቅምት 2013 ዓ. በትግራይ ክልል የተጀመረው ግጭት፣ መንግስት ግጭቱ ከተጀመረ ከ8 ወራት በኋላ የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፤ሰራዊቱን ቢያስወጣም ግጭቱ ሊያቆም አልቻለም፡፡
በሽብር የተፈረጀው ህወሓት በአማራና አፋር ክልል ጥቃት በመክፈት የተወሰኑ የአማራ ክልል ቦታዎችን በቁጥጥሩ ስር ማድረጉንና በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት እንዳልሰነዘረ ገልጿል፡፡
የፌደራል መንግስት የህወሓት ኃይሎች በአማራና በአፋር ክልል በፈጸሙት ጥቃት ንጹሃን መሞታቸውን ከ300ሺ በላይ ሰዎች ከቀያቸው መፈናቀላቸውን መግለጹ ይታወሳል፡፡