ህወሓት በደብረታቦር በፈጸመው የከባድ መሳሪያ ጥቃት የአንድ ቤተሰብ አባላት ናቸው የተባሉ 5 ሰዎች መሞታቸው ተነገረ
በጥቃቱ በ2 ሰዎች ላይ ከባድ ጉዳት እንደደረሰ እና ግምቱ ያልታወቀ ንብረት እንደወደመም ተነግሯል
ከተገደሉት መካከል ህጻን ይገኝበታል ተብሏል
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት የፈረጀው ህወሓት በደብረታቦር ከተማ ከባድ መሳሪያዎችን በመጠቀም በፈጸመው ጥቃት 5 ሰዎችን መግደሉን የከተማ አስተዳደሩ ተቀዳሚ ከንቲባ አቶ ወንዴ መሰረት አስታወቁ፡፡
በጥቃቱ የተገደሉት አንድን ህጻን ጨምሮ የአንድ ቤተሰብ አባላት የሆኑ 3 ሴቶችና 2 ወንዶች ናቸው።
ተቀዳሚ ከንቲባው በአራት ከባድ መሳሪያዎች የተፈጸመ ነው ባሉት ጥቃት በ2 ሰዎች ላይ ደግሞ ከባድ ጉዳት እንደደረሰ እና የግለሰቦች ቤትን ጨምሮ ግምቱ ያልታወቀ ንብረት መውደሙን ተናግረዋል፡፡
አቶ ወንዴ የአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎችን የተቆጣጠረው ህወሓት ጥቃቱን የፈጸመው “በደቡብ ጎንደር ዞን በከፈተው ውጊያ ከሀገር መከላከያ፣ አማራ ልዩ ኀይል፣ ሚሊሻ እና ፋኖ እየደረሰበት ያለውን ኪሳራ መቋቋም ሲያቅተው በተስፋ መቁረጥ” ነው ሲሉ መናገራቸውን የአማራ ሚዲያ ኮርፖሬሽን ዘግቧል፡፡
የሃገር መከላከያ ሰራዊትን ከመቀሌ ለቆ መውጣት ተከትሎ ወደ መቀሌ የተመለሰው የህወሓት ኃይል በመንግስት የታወጀውን የተናጠል ተኩስ አቁም ባለመቀበል በተለያዩ የአማራ እና የአፋር ክልል አካባቢዎች ጥቃቶችን ፈጽሟል፡፡
ባደረጋቸው የተለያዩ ዘመቻዎችም ወደ አማራ ክልል ገብቶ አንዳንድ የሰሜን ወሎ እና የደቡብ ጎንደር አካባቢዎችን ተቆጣጥሯል፡፡
በፈጸማቸው ጥቃቶች የበርካቶች ህይወት ሲያልፍ ከ500 ሺ በላይ ዜጎች ደግሞ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል፡፡
ይህን ተከትሎ የአማራ ክልል አቅም ያለውና የቻለው ሁሉ እንዲዋጋ ክተት አውጆ ዘመቻዎችን በማድረግ ላይ ነው፡፡
ተኩስ አቁሙ አለመከበሩን ያስታወቀው የፌዴራል መንግስትም ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ አቅጣጫ አስቀምጦ ጦርነት እየተካሄደ ይገኛል፡፡
ህወሓት “ዋና ዓለማው ይሄን ክልል ማዳከም ነው ይህን በዋናነት ቀደም ብሎም ሲሰራው ነበር” ያሉት የአማራ ልዩ ኀይል ዋና አዛዥ ብርጋዴር ጀኔራል ተፈራ ማሞ “በገባባቸው የተለያዩ የአማራ ክልል አካባቢዎች እየተመታ ነው በመዳከምም ላይ ይገኛል” ሲሉ ትናንት ከጋዜጠኞች ጋር በነበራቸው ቆይታ ተናግረዋል፡፡
በጋይንት በኩል የመጣው ሃይል ተመቶ ወደፊት ሊቀጥል በማይችልበት ደረጃ ላይ መድረሱንም ነው አዛዡ የተናገሩት፡፡
ከአሁን በኋላ ይህን ኃይል እስከ መጨረሻው ለማዳከም ወደ ማጥቃት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡ ይህ ካልሆነ ሃገር ችግር ላይ ትወድቃለችም ነው ያሉት፡፡
በጥቅምት ወር 2013 የህወሓት ሃይሎች በትግራይ ክልል በሚገኘው የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጀው የህግ ማስከበር ዘመቻ የተጀመረው ግጭት አሁን ላይ 11 ወራት ሊሆነው ነው፡፡