የቀድሞው የሐዋሳ ከንቲባ ጠባቂ በጠለፋ ወንጀል የ16 ዓመት እስር ተፈረደበት
ግለሰቡ በአስገድዶ መድፈር እና ጠለፋ ወንጀል ተከሶ ጥፋተኛ ሆኖ ተገኝቷል
የፖሊስ ባልደረባው ባሳለፍነው ዓመት ግንቦት ወር ላይ ጸጋ በላቸው የተባለች ሴትን ጠልፎ ከተሰወረ ከቀናት በኋላ በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋሉ ይታወሳል
የቀድሞው የሐዋሳ ከንቲባ ጠባቂ የነበረው እና ጠለፋ የፈጸመው ሳጅን የኋላመብራቴ ወ/ማሪያም የ16 ዓመት እስር ተፈረደበት
በሲዳማ ክልል ዳሽን ባንክ ሐዋሳ ዋርካ ቅርንጫፍ አካውንታት ሆና ስትሰራ የቆየችው ወይዘሪት ጸጋ በላቸው ግንቦት 15 ቀን 2015 ዓ.ም አመሻሽ ላይ ከስራ ወደ ቤቷ ለማምራት ታክሲ በምትይዝበት ቦታ ላይ መጠለፏ ይታወሳል፡፡
ጠላፊው ሳጅን የኋላመብራቴ ወ/ማሪያም የሚባል ሲሆን የቀድሞ የሀዋሳ ከተማ ከንቲባ የአቶ ጸጋዬ ቱኬ የግል ጠባቂ እንደነበረ በወቅቱ ተገልጾም ነበር፡፡
ይህ ሕግ አስከባሪ ግለሰብ የግል ተበዳይ የሆነችውን ፀጋ በላቸውን በመጥለፍ ለቀናት ተሰውሮ ከቆየበት ቦታ በፖሊስ እና ህዝብ ትብብር በሕግ ቁጥጥር ስር እንደዋለም አይዘነጋም፡፡
ተጠርጣሪው ከተያዘ በኋላ ምርመራዎች ሲካሄዱ ቆይቶ በጠለፋ እና አስገድዶ በመድፈር የወንጀል ድርጊት ክስ ተመስርቶበት የሕግ ክርክር ሂደቱ ላለፉት ወራት ሲካሄድ ቆይቷል፡፡
ንግድ ባንክና አቢሲኒያ ባንክ፣ ጨምሮ 16 ባንኮች እንደተጭበረበሩ ፍትህ ሚኒስቴር ገለጸ
የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ እንዳስታወቀው ሳጅን የኋላመብራቴ የግል ተበዳይ የሆነችውን ፀጋ በላቸውን በመጥለፍና አስገድዶ በመድፈር የተከሰሰበት መዝገብ በሀዋሳ ከተማ የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት ቀርቦ ሲያከራክር መቆየቱን ገልጿል፡፡
ፍርድ ቤቱ የከሳሽ ዓቃቤ ህግ ያቀረበውን ማስረጃ በመስማት ተከሳሽ በ1ኛ ክስ የወንጀል ህግ አንቀፅ 37 እና 587(1) መሰረት እንዲከላከል እንዲሁም በሁለተኛ ክስ በ620 (3) መሰረት እንዲከላከል ብይን ቢሰጥም ተከሳሽ ጥፋቱን ባለማስተባበሉ ፍርድ ቤቱ ተከሳሹን ጥፋተኛ ብሎታል፡፡
በዚሁ መሰረትም የሀዋሳ ከተማ መጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት በቀን 18/04/2016 ዓ.ም በዋለው የሴቶችና ህጻናት ችሎት የቅጣት ማክበጃ እና ማቅለያ ሁኔታዎችን በማየት በተከሳሹ ላይ ውሳኔ አስተላልፏል፡፡
በውሳኔው መሰረትም ተከሳሽ ሳጅን የኋላመብራቴ ወ/ማሪያምን በ16 ዓመት ጽኑ እስራት እንዲቀጣ እንደተወሰነበት የሲዳማ ክልል ፍትህ ቢሮ ገልጿል፡፡