የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን ባለሙያዎች በግድቡ የቴክኒክ እና የሕግ ጉዳይ ዙሪያ ውይይት እንደሚያደርጉ ይጠበቃል
ሶስተኛው ዙር የሕዳሴው ግድብ ሶስትዮሽ ውይይት በግብጽ ተጀመረ፡፡
ጠቅላይ ሚንስትር አብይ አህመድ ባሳለፍነው ሀምሌ ግብጽ በሱዳን ጉዳይ ለመምከር በካይሮ በተካሄደው የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ ባመሩበት ወቅት ከግብጽ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አልሲሲ ጋር በኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዙሪያ መወያየታቸው ይታወሳል።
የሁለቱ ሀገራት መሪዎችም በሕዳሴ ግድብ ዙሪያ በአራት ወራት ውስጥ ወደ ስምምነት ለመምጣት በተስማሙት መሰረት የኢትዮጵያ፣ ግብጽ እና ሱዳን የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይታቸውን ካሳለፍነው ነሀሴ ጀምሮ በማካሄድ ላይ ናቸው፡፡
የቴክኒክ ባለሙያዎች ውይይት በሶስቱ ሀገራት ዋና ከተሞች እንዲደረግ የተስማሙ ቢሆንም ሱዳን በገጠማት የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ውይይቱን ማስተናገድ አልቻለችም፡፡
የመጀመሪያው የሶስትዮሽ የባለሙያዎች ውይይት በግብጽ ካይሮ ሲካሄድ ሁለተኛው ደግሞ ከ20 ቀናት በፊት በአዲስ አበባ ተካሂዶም ነበር፡፡
ስለ ህዳሴው ግድብ የኮርቻ ግድብ ምን ያህል ያውቃሉ?
ሶስተኛው ተመሳሳይ ውይይት ዛሬ በግብጽ ካይሮ በመካሄድ ላይ መሆኑን በህዳሴው ግድብ የኢትዮጵያ የባለሙያዎች ቡድን መሪ እና በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለሺ በቀለ በቀድሞ ስሙ ትዊተር ወይም ኤክስ አካውንታቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
አምባሳደሩ በጽሁፋቸው ላይ አክለውም “3ኛውን ዙር የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የውሃ ሙሌት እና አለቃቀቅ ደንቦችና መመሪያዎች የሶስትዮሽ ድርድር በካይሮ ጀምረናል:: በድርድሩም ባልተፈቱ የቴክኒካል እና የህግ ማእቀፍ ጉዳዮች የተሻለ ውጤት ላይ ለመድረስ ትኩረት ይደረጋል” ብለዋል::
ከ12 ዓመት በፊት የተጀመረው የታላቂ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ አጠቃላይ ግንባታው 91 በመቶ ደርሷል ተብሏል።
ኢትዮጵያዊያን በሚያዋጡት ገንዘብ እና በመንግስት ወጪ እየተገነባ ያለው ይህ ግድብ በ5ሺህ 200 ሜጋ ዋት ሀይል በማመንጨት ከአፍሪካ ትልቁ ፕሮጀክት ነው።
የህዳሴው ግድብ ሁለት ተርባይኖች እያንዳንዳቸው 350 ሜጋ ዋት ሀይል ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ሀይል በማመንጨት ላይ ይገኛል።
ግድቡ እስካሁን ከ180 በላይ ቢሊዮን ብር ወጪ የተደረገበት ሲሆን ቀሪ ግንባታውን ለማጠናቀቅ 60 ቢሊዮን ብር እንደሚያስፈልግ ተገልጿል።
የህዳሴው ግድብ ከሁለት ዓመት በኋላ ሙሉ ለሙሉ ይጠናቀቃል የተባለ ሲሆን አሁን ላይ ከ40 ቢሊዮን በላይ ሜትር ኪዩብ ውሀ በግድቡ ውስጥ ይገኛል ተብሏል።