ኢራን አጋሮቿን አስተባብራ በእስራኤልና በአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያዎች ላይ የተቀናጀ እርምጃ ትወስዳለች መባሉ የቀጠናውን ውጥረት አባብሶታል
በኢራቅ የሚገኘው የአሜሪካ ወታደራዊ ጣቢያ የሮኬት ጥቃት ተፈጸመበት።
በሮኬት ጥቃቱ በጥቂቱ አምስት ወታደሮች መቁሰላቸም ነው የተነገረው።
በምዕራባዊ ኢራቅ በሚገኘው ወታደራዊ ጣቢያ ላይ ሁለት ሮኬቶች መተኮሳቸውን የኢራቅ ባለስልጣናትን ጠቅሶ ሬውተርስ ዘግቧል።
ጥቃቱ አሜሪካ በኢስማኤል ሃኒየህ ግድያ በተዘዋዋሪም ቢሆን እጇ አለበት ያለችው ኢራን እወስደዋለሁ ካለችው የአጻፋ እርምጃ ጋር ስለመያያዙ ግን አልታወቀም።
ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የአሜሪካ ባለስልጣን በኢራቅ በተፈጸመው ጥቃት ጉዳት ከደረሰባቸው ውስጥ አንዱ ለህይወቱ አስጊ ሁኔታ ውስጥ እንደሚገኝና የቆሰሉት ቁጥርም ከፍ ሊል እንደሚችል ይጠበቃል ብለዋል።
ጥቃቱ እስራኤል በሊባኖስና ኢራን መዲናዎች የሄዝቦላህና ሃማስ ከፍተኛ መሪዎችን መግደሏን ተከትሎ ቴህራን እወስደዋለሁ ያለችው የበቀል እርምጃ ዋሽንግተንንም ሊያካትት እንደሚችል አመላክቷል።
የጋዛ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በኢራቅ፣ ሶሪያ፣ የመንና ሊባኖስ የሚገኙና ኢራን ድጋፍ የምታደርግላቸው ታጣቂዎች በአሜሪካ ወታደራዊ ይዞታዎች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ መቆየታቸው ይታወሳል።
ተጨማሪ የጦር መርከቦችና ተዋጊ ጄቶችን ወደ መካከለኛው ምስራቅ እልካለሁ ያለችው ዋሽንግተን ከቴህራን ጋር መልካም ግንኙነት ያላት ባግዳድ ውጥረቱን በማርገብ ሂደት እንድታግዛት ጠይቃለች።
የአሜሪካው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒ ብሊንከንም ለኢራቁ ጠቅላይ ሚኒስትር ሞሀመድ ሺያ አል ሱዳኒ ደውለው ቴህራንን እንዲያግባቡ ጠይቀዋቸዋል ነው የተባለው።
በቀጠናው በልዩነት የኢራንም የአሜሪካም አጋር በሆነችው ኢራቅ 2 ሺህ 500 የአሜሪካ ወታደሮች ይገኛሉ።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ አንስቶ በአሜሪካ ወታደሮች ላይ ያነጣጠሩ ተደጋጋሚ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።
ባግዳድ የጥቃት ማዕከል የሆኑት የአሜሪካ ወታደሮች ከመጪው መስከረም ወር ጀምሮ ከሀገሪቱ እንዲወጡና በአንድ አመት ወታደራዊ ጣቢያው እንዲዘጋ ትፈልጋለች ተብሏል።