የፈረንሳይና የጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቀጣዩ ሳምንት ኢትዮጵያን ይጎበኛሉ
ሚኒስትሮቹ በሰሜን ኢትዮጵያ ሰላም ለማስፈን የተደረሰው ስምምነት ተፈጻሚነትን ለመደገፍ ነው በጋራ አዲስ አበባ የሚገቡት
የአውሮፓ ሀገራት ከኢትዮጵያ እና የአፍሪካ ህብረት ጋር በሚኖረው ግንኙነት ዙሪያም ምክክር ያደርጋሉ ተብሏል
የፈረንሳይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ካትሪን ኮሎና በቀጣዩ ሳምንት ኢትዮጵያን እንደሚጎበኙ ተናግረዋል።
የጀርመን አቻቸው አባሌና ባርቦክም አብረዋቸው አዲስ አበባ እንደሚገቡ ሚኒስትሯ አል ሲ ኤል ለተባለ የቴሌቪዥን ጣቢያ ገልጸዋል።
የጉዟችው ዋነኛ አላማም የፌደራል መንግስት እና ህውሃት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የደረሱት ስምምነት ተፈጻሚነት ማጠናከር መሆኑን ነው ያነሱት።
ፈረንሳይና ጀርመን የአፍሪካ ህብረት እያካሄደ ያለውን የሰላም ጥረት መደገፍ በሚችሉበት ሁኔታ ላይም ምክክር ይደረጋል ብለዋል ሚኒስትሯ ካትሪን ኮሎና።
አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ እንደዘገበው ሁለቱ ሚኒስትሮች በኢትዮጵያ የሁለት ቀናት ቆይታን ያደርጋሉ (ከጥር 4 እስከ 5 2015)።
በሚኒስትሮቹ ጉብኝት ፓሪስ እና በርሊን ለኢትዮጵያ የሰብአዊ ድጋፍ ለማድረግ ቃል እንደሚገቡም ይጠበቃል ብሏል አፍሪካ ኒውስ።
ከዚህ ባሻገር ሀገራቱ ከኢትዮጵያ ብሎም ከአፍሪካ ህብረት ጋር ግንኙነታቸውን የሚያጠናክሩ ውይይቶችን ያደርጋሉ ተብሏል።
ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት አመታት በሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ከምዕራባውያን ሀገራት ጋር ግንኙነቷ ሻክሮ መቆየቱ ይታወቃል።
በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ከተፈረመና በኬንያ ናይሮቢ ተከታታይ ስምምነቱን ማስፈጸሚያ ምክክሮች ተደርገው በትግራይ ሰላም መስፈን ከጀመረ ወዲህ ግን ሻክሮ የቆየው ግንኙነት መለሳለስ መጀመሩ እየታየ ነው።
የፈረንሳይ እና ጀርመን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቀጣይ ሳምንት በኢትዮጵያ የሚያደርጉት ጉብኝትም የዚሁ ማሳያ ተደርጎ ሊወሰድ ይችላል።