የሰርጓጅ መርከቦችን ስምምነት በተመለከት የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር “ዋሽተውኛል”- ኢማኑኤል ማክሮን
የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትርም “ለፕሬዝዳንቱ ምንም ነገር አልዋሸሁም” ሲሉ ተደምጠዋል
አውስትራሊያ ከፈረንሳይ ጋር የነበራትን የባህር ሰርጓጅ መርከቦች ግዥ ውል መሰረዟ ፈረንሳይን አበሳጭቷል
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑእል ማክሮን የተሰረዘውን የሰርጓጅ መርከብ ግዢ ስምምነት በተመለከተ የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ማሪሰን “ዋሽተውኛል” ብለዋል።
አውስትራሊያ ከፈረንሳይ ጋር የነበራትን የባህር ሰርጓጅ (ሰብማሪን) መርከቦች ግዥ ውል መሰረዟን ተከትሎ የሁለቱ ሀገራት ግንኙነት መሻከሩ ይታወሳል።
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑእል ማክሮን አውስትራሊያ ከፈረንሳይ ጋር የነበራት የ37 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ዶላር የባህር ሰርጓጅ (ሰብማሪን) መርከቦች ግዥ ስምምነት በመሰረዝ ከአሜሪካና ብሪታኒያ ጋር አዲስ ወታደራዊ ማእቀፍ ስምምነት በመፈራረሟ ተበሳጭተው ነበር።
ከስምምነቱ መሰረዝ በኋላም የፈረንሳዩ ፕሬዚዳንት ኢማኑእል ማክሮን እና የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ማሪሰን በጣሊያኗ ሮም እየተካሄደው ካለው የቡድን 20 ሀገራት ጉባዔ ላይ መገናኘታቸው ተነግሯል።
ከቡድን 20 ጉባዔ ጎን ለጎን ለፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑእል ማክሮን “ከዚህ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ማሪሰን ያምሉ” የሚል ከጋዜጠኞች ጥያቄ የቀረበላቸው ሲሆን፤ “ ሞሪሰን የሚያመጣውን ውጤት በጋራ የምናይ ይሆናል” ብለዋል።
“ለሀገሪቱ እና ለመላው የአውስትራሊያ ህዝብ ክብር አለኝ፤ በሀገሪቱ ህዝብ ጋርም በርካታ ወዳጅነት አለን” ያሉት ፕሬዝዳንት ማክሮን፤ እኛ ስናከብራችሁ እናንተም እውነተኛ እና ከእኛ ጋር በአግባቡ መስራት አለባችሁ” ብለዋል።
የፕሬዝዳንት ማክሮንን አስተያየት ተከትሎ የአውስትራሊያው ጠቅላይ ሚኒስትር ስኮት ማሪሰን በሰጡት ምለሽ፤ “ለፕሬዝዳንቱ ምንመ ነገር አልዋሸሁም፤ ከዚህ በኋላ መደበኛ ሰርጓጅ መርከቦች ለአውስትራሊያ እንደማያስፈልጓት በስነ ስርዓት አስረድጃቸዋለሁ” ብለዋል።
በፈረንሳይ መካከል የሻከረውን ግንኙነት እና እምነት መልሶ ለመገንባት ስራዎች መጀመራቸውንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት።
አውስትራሊያ ከፈረንሳይ ጋር የነበራትን የባህር ሰርጓጅ (ሰብማሪን) መርከቦች ግዥ ውል በመሰረዟ በፈረንሳይ፣ በአውስትራሊያ እና በአሜሪከ መካከል ከፍተኛ የሆነ ቅራኔን ፈጥሮ ቆይቷል።
የፈረንሳዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጄያን ለቨድሪያን በወቀቱ በሰጡት አስተያየት የአውስትራሊያ ተግባር “በወዳጅ ከጀርባ በስለት እንደመወጋት ነው” ብለው ነበር።
አውስትራሊያ ስምምነቱን ሰርዛ ከአሜሪካ እና ከብሪታኒያ ጋር አዲስ የወታደራዊ ማእቀፍ ስምምነት በመፈረሟ የተበሳጨችው ፈረንሳይ በአሜሪካ እና በአውስትራሊያ የሚገኙ አምባሳደሮቿን ጠርታ እንደበረም ይታወሳል።
አውስትራሊያ እና ፈረንሳይ በአውሮፓውያኑ በ2016 ነበር የባህር ሰርጓጅ (ሰብማሪን) መርከቦች ግዢ ስምምነት የተፈራረሙት፤ በስምምነቱ መሰረትም ፈረንሳይ 12 የባህር ሰርጓጅ (ሰብማሪን) መርከቦች ለአውስትራሊያ ለመገንባ ተስማምተው ነበር።