ምዕራባውያን “ዓለምን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ሙከራ” ማብቂያ ተቃርቧል - ፑቲን
“ለሉዓላዊነታችን እና ለልጆቻችን ወደፊት” ስንል የምናካሂደው ነው ሲሉም ስለ ጦርነቱ ገልጸዋል ፕሬዝዳንቱ
ቭላድሚር ፑቲን ሊከፋሉን ይሞክራሉ ላሏቸው ምዕራባውያን ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለኃያል ምዕራባዊ ሃገራት ማስጠንቀቂያ ሰጡ፡፡
ከዳተኞች ላሏቸው ለኃያል ነን ባይ ምዕራባዊ ሃገራት ጠንከር ያለ ማስጠንቀቂያን የሰጡት ፕሬዝዳንቱ ዓለምን በበላይነት ለመቆጣጠር የሚያደርጉት ሙከራ ማብቂያ ተቃርቧል ብለዋል፡፡
ፑቲን ሶስት ሳምንት ያስቆጠረውን ዬክሬን ጦርነት በተመለከተ ጠንከር ያለ መግለጫ ሰጥተዋል፡፡
በመግለጫቸው እዛ እየኖሩ እዚህ በሚከፈላቸው 5ኛ ረድፈኞች (5th columnists) በኩል ሊከፋፍሉን ሊሞክሩ ይችላሉ ያሉት ፑቲን ለዚህም ግጭትና ብጥብጥን የሚፈጥሩና የሚከፋፍሉ የምዕራባውያኑ ስውር ተከፋይ 5ኛ ረድፈኞች አሉ ብለዋል፡፡ የዚህ ዓላማው ሩሲያን መጣል እንደሆነም ነው የተናገሩት፡፡
ጦርነቱ ቀድሞውኑ ጠንካራ እና ሉዓላዊት ሩሲያ እንዳትፈጠር ይፈልጉ ለነበሩት ምዕራባውያን ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩንም ነው የተናገሩት ፑቲን፡፡
“ለሉዓላዊነታችን እና ለልጆቻችን ወደፊት” ስንል የምናካሂደው ነው ሲሉም ስለ ጦርነቱ ገልጸዋል፡፡
ፑቲን ዩክሬን “ተጠናውቷታል” ያሉትን ‘የናዚ መንፈስ’ ለማጽዳት በሚል ነው ከሶስት ሳምንት በፊት ጦርነቱ እንዲጀመር ያዘዙት፡፡
ከዚያም ወዲህ ምዕራባውያኑ ከዓለም አቀፍ የፋይናንስ እንቅስቃሴዎች ማገድን ጨምሮ በርካታ ማዕቀቦችን በሩሲያ ላይ አዝንበዋል፡፡ የኢኮኖሚዋ የደም ስር ነው በማለትም ነዳጅ ከሩሲያ መግዛታቸውን ማቆማቸውንም አስታውቀዋል፡፡
ሆኖም ይህ የምዕራባውያኑ እርምጃ እንደማይገታቸው ነው ፑቲን ያስታወቁት፡፡ ሃገራቸው ወደ ጦርነቱ ያስገባትን ዓላማ ሳታሳካ እንደማትመለስም ደጋግመው ገልጸዋል፡፡
ጦርነቱ ቀደም ሲልም በያዝነው ውጥን መሰረት በውጤታማነት እየሄደ ነው ያሉም ሲሆን ምዕራባውያኑ የእርስ በርስ ግጭትን ለመቀስቀስ እየሞከሩ መሆኑንም በመጠቆም፤ የማዕቀብ ጋጋታ ሊጎዳን ቢችልም ዜጎቻችንን እንደግፋለን፤ የፖሊሲ ለውጦችን እናደርጋለን ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡
ትናንት ለአሜሪካ ህግ መወሳኛ ምክር ቤት ጦርነቱን የተመለከተ ማብራሪያ የሰጡት የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቬሎዶሚር ዜሌንስኪ በበኩላቸው ሩሲያ አውሮፓ ላለፉት 80 ዓመታት አይቶት የማያውቀውን ወረራ ነው የፈጸመችው ብለዋል፡፡
ሃገራቸው በጃፓን ከተፈጸመው የፐርል ሃርበር ጥቃት እና ከመስከረም 11ዱ የሽብር ጥቃት ያልተናነሰ ችግር እንደገጠማትም ነው ዜሌኒስኪ ለምክር ቤቱ አባላት የተናገሩት፡፡