አሜሪካ ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ ለ12 ጊዜ ዜጎቿ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ አስጠንቅቃለች
ሀገሪቱ ማስጠንቀቂያውን ያወጣችው የኢትዮጵያ የጸጥታ ሁኔታ እየተባባሰ ነው በሚል ነው
የገንዘብ ችግር ያለባቸው አሜሪካዊያን የጉዞ ቲኬት በብድር እንዲገዙም አሰራር ዘርግታለች
አሜሪካ ባለፉት 10 ቀናት ውስጥ ለ12 ጊዜ ዜጎቿ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ አስጠንቅቃለች።
በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ በህወሓት መጠቃቱን ተከትሎ ነበር በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የተጀመረው።
ይሄንን ተከትሎም ህወሓት በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሽብርተኝነት ከመፈረጁ በፊት የአገር መከላከያ ሰራዊት እርምጃ ለመውሰድ ወደ ትግራይ ክልል ከገባ ከስምንት ወራት በኋላ የተናጠል ተኩስ አውጆ ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች መመለሱም አይዘነጋም።
ከዚህ ውሳኔ በኋላም ህወሓት ወደ አማራ እና አፋር ክልሎች አዲስ ጥቃት የከፈተ ሲሆን በተለያዩ የውጊያ ግምባሮች ጥቃቶችን ከፍቶ በርካቶችን በማፈናቀል ንብረት እና መሰረተ ልማቶችን አውድሟል።
ህወሓት በተለይም በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ያሉትን ደሴ እና ኮምቦልቻ ከተሞችን ከተቆጣጠረ በኋላ አሜሪካ ዜጎቿ ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ በተደጋጋሚ አሳስባለች።
ከህዳር 18 ቀን 2014 ዓ.ም አንስቶ እስከ ትናንት ድረስ ባሉት 10 ቀናት ውስጥ 12 ጊዜ አሜሪካዊያን ኢትዮጵያን ለቀው እንዲወጡ አሳስባለች።
በኢትዮጵያ ያለው የጸጥታ ሁኔታ እየተባባሰ መምጣቱ አሜሪካዊያን አዲስ አበባን ለቀው እንዲወጡ በምክንያትነት በማሳሰቢያው ላይ ተገልጿል።
ከዚህ ባለፈም ከኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ዜጎች የጉዞ ቲኬት ምግዣ የገንዘብ ችግር ከገጠማቸው ብድር መዘጋጀቱንም በአዲስ አበባ ያለው የአሜሪካ ኢምባሲ በተደጋጋሚ ባወጣቸው መግለጫዎቹ ላይ ጠቅሷል።
በተጨማሪም በኢትዮጵያ የሽብር ፅቃጽ ሊፈፀም ስለሚችል ዜጎቿ ወደ ገበያ ማእከላት እና ህዝብ ወደ ሚሰበሰብባቸው ስፍራዎች ከመሄድ እንዲቆጠቡ አሳስባ እንደነበረም አይዘነጋም።
በአስቸኳይ ኢትዮጵያን ለቀው ይውጡ የሚለው የአሜሪካ ተደጋጋሚ ማሳሳቢያ በኢትዮጵያ መንግስት እና ኢትዮጵያዊያን ተቃውሞ ገጥሞታል።
የኢትዮጵያ መንግስት አሜሪካ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን ጸጥታ አስመልክቶ የሚያወጣውን መግለጫ እንዲያቆም ማሳሰቡ ይታወሳል።
የመንግስት ኮሙንኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ከበደ ዴሲሳ “አሜሪካ ከፈለገች ዜጎቿን ማስወጣት ትችላለች” ነገር ግን የኢትዮጵያ የደህንነት ሁኔታ በየጊዜው እየተሻሻለ መጥቷል ሲሉ ተናግረው አሜሪካ ከምታወጣቸው ያልተገቡ የለቃችሁ ውጡ መግለጫዎች እንድትታቀብ ማስጠንቀቃቸው ይታወሳል።
መንግስት የህወሃት ሃይሎችን ወደ አማራና አፋር ክልሎች መስፋፋት ተከትሎ በሀገር ላይ ደቅነውታል ያለውን አደጋ ለመቀልበስ በማስብ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጁ ይታወሳል።
ከሁለት ሳምንት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ግንባር ከዘመቱ በኋላ የህወሓት ሃይሎች ይዘዋቸው የነበሩትን በርካታ የመንግስት ሃይሎች ማስለቀቅ ችለዋል።