በአቶ ጌታቸው የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር በደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን መፈንቅለ መንግስት አውጆብኛል ሲል ከሰሰ
በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ባወጣው መግለጫ አቶ ጌታቸው ረዳን ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንትነት "አንስቻለሁ" ብሏል
ጊዜያዊ አስተዳደሩ "በአጥፊ ኃይሉ" ላይ እርምጃ በሚወስድበት ወቅት ለሚፈጠር ችግር ኃላፊት የሚወስደው የዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን ብቻ ነው ብሏል
በአቶ ጌታቸው የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር በደብረጽዮን የሚመራው የህወሓት ቡድን መፈንቅለ መንግስት አውጆብኛል ሲል ከሷል።
በዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ቡድን ትናንት ረፋድ ባወጣው መግለጫ አቶ ጌታቸው ረዳን ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንትነት "አንስቻለሁ" ብሏል።
ይህን ተከትሎ አቶ ጌታቸው በሚመሩት የህወሓት ቡድን የሚመራው የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ የዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን ይፋዊ መፈንቅለ መንግስት አውጆብኛል ሲል ከሷል።
በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ቡድን በጊዜያዊ አስተዳደሩ ላይ አደረኩት ባለው ማሻሻሻያ አምስት የካቢኔ አባላትን፣ ሁለት የቢሮ ኃላፊዎችን እና ሰባት የዞን አስተዳዳሪዎችን ከኃላፊነት ማንሳቱን አስታውቋል።
እነዚህ የጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች መምራት፣ መወሰን እና መወከል አይችሉም ያለው ይህ ቡድን አቶ ጌታቸው በማን እና እንዴት እንደሚተኩ ከፌደራል መንግስት ጋር እየመከረበት እንደሆነ ገልጿል።
በአቶ ጌታቸው የሚመራው ጊዜያዊ አስተዳደር በመግለጫው የዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን ከባለፈው መስከረም ጀምሮ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ያለውን ፍላጎት በይፋ ገልጿል፤ በትግራይ ትርምስ የመፍጠር አላማ አለው ብሏል።
የዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን ባለፈው ነሐሴ ወር ካካሄደው "ህገወጥ ጉባኤ" ወዲህ ህግና ስርአት እየጣሰ መሆኑን የገለጸው ጊዜያዊ አስተዳደሩ "በትግራይ ጦር እና በጊዜያዊ አስተዳደሩ አመራሮች ላይ የስም የማጥፋት ዘመቻ ከፍቷል" ሲልም ከሶታል።
ጊዜያዊ አስተዳደሩ ይህን ተግባር እንደማይታገስ እና "በአጥፊ ኃይሉ" ላይ እርምጃ በሚወስድበት ወቅት ለሚፈጠር ችግር ኃላፊት የሚወስደው ይህ ቡድን ብቻ ነው ብሏል።
ህወሓት ወደ ሁለት ቡድን የተከፈለው በዶ/ር ደብረጽዮን የሚመራው ቡድን ባለፈው ነሐሴ ወር "የመዳን ጉባኤ" ሲል የሰየመውን 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ማካሄዱን ተከትሎ ነው። ቡድኑ በወቅቱ ጉባኤውን ያደረገው የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸውን ጨምሮ 17 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት እና ምርጫ ቦርድ ጉባኤ እንዳያካሄድ ያደረጉትን ጥሪ ወደ ጎን በመተው ነበር።
የዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን በጉባኤው ምክትል ሊቀመንበር የነበሩትን አቶ ጌታቸውን በአቶ አማኑኤል አሰፋ በመተካት እና ዶ/ር ደብረጽዮንን በድጋሚ በመምረጥ ነበር ያጠናቀቀው።
ምርጫ ቦርድ ለጉባኤው እና በጉባኤው ለተላለፉ ውሳኔዎች እውቅና እንደማይሰጥ መግለጹ ይታወሳል።
በዶ/ደብረጽዮን እና በአቶ ጌታቸው በሚመሩት ሁለት የህወሓት ቡድኖች መካከል ያለው እስጣገባ ግን ከዚህ ጉባኤ በኋላ እየተባባሰ መጥቷል።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ የዶ/ር ደብረጽዮን ቡድን አቶ ጌታቸውን ጨምሮ 16 አመራሮች ይቅርታ እንዲጠይቁ የተጠሳቸው የአንድ ወር ጊዜ ስለተጠናቀቀ ከፖለቲካ እና ከፓርቲ ስራዎች እንዳገዳቸው መግለጹ ውጥረቱን አባብሶታል።
ቡድኑ እንደገለጸው የታገዱት አመራሮችም ህወሓትን ወክለው በጊዜያዊ አስተዳደሩ ውስጥ ውሳኔ የመስጠት መብት እንደሌላቸው ገልጾ ነበር።
አንደኛው ቡድን ሌላኛው ያሳለፈውን ውሳኔ ውድቅ እያደረገ ችግሩ መፍትሄ ሳያገኝ ቀጥሏል።
የሁለቱ ቡድኖች አመግባባት ወደ ግጭት እንዳይገባ የትግራይ የጸጥታ ኃይል እጁን እንዳያስገባ ጥሪ መቅረቡ ይታወሳል።