ህወሓት አቶ ጌታቸው ረዳን ለጊዜያዊ መንግስት ፕሬዝዳንትነት እጩ አድረጎ መረጠ
አቶ ጌታቸው ለረጅም ጊዜያት የህወሓት ቃል አቀባይና የፕሬዝዳንት አማካሪ ሆነው በመስራት ይታወቃሉ
ምርጫው ፌዴራል መንግስት ተቀባይነት ስለማግኘቱ የተረጋገጠ ነገር የለም
ህወሓት መጋቢት 8 ቀን 2015 ባካሄደው ስብሰባው አቶ ጌታቸው ረዳን ለጊዜያዊ መንግስት ፕሬዝዳንትነት እጩ አድረጎ መምረጡ የድርጅቱ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ፕሮፌሰር ክንደያ ገ/ህይወት በትዊተር ገጻቸው ባጋሩት ጽሁፍ አስታውቀዋል፡፡
41 አባላት ያሉት የህወሓት መአከላዊ ኮሚቴ አቶ ጌታቸውን የመረጠው ሰባት እጩዎችን ለምርጫ ካቀረበ በኋላ ነው ተብሏል ፡፡
አል ዐይን ከምንጮቹ እንዳረጋገጠው ፍስሃ ሃፍተጽዮን (ዶ/ር) ፣ኪሮስ ጉዕሽ (ዶ/ር) እና አማኑኤል ሃይለ (ዶ/ር) በህወሓት ስራ አስፈጻሚ በኩል እጩ ሆነው የቀረቡ ሲሆን አቶ ጌታቸው ረዳ፣ ክንደያ ገብረሂወት (ፕሮፌሰር) ፣ሓጎስ ጎደፋይ (ዶ/ር) እና አቶ ረዳኢ ሃለፎም በተሳታፊው ተጠቁመዋል፡፡
በመጨረሻም ማአከላዊ ኮሚቴው በሰጠው ድምጽ አቶ ጌታቸው ረዳ በ18 ድምጽ አንደኛ እንዲሁም ፍስሃ ሃፍተጽዮን በ17 ድምጽ ሁለተኛ ሆነው ተመርጠዋል ፡፡
የተቀሩት ከሶስት አስከ ዜሮ ያለውን ድምጽ አግኝተዋል፡፡
ህወሓት ለረጅም አመታት ድርጅቱን ቃል አቀባይና የፕሬዝዳንት አማካሪ ሆነው የሰሩትን አቶ ጌታቸው ረዳን ቢመርጥም በፕሪቶሪያው ስምምነት መሰረት የፌዴራል መንግስት ይሁንታ ማግኘት ይኖርበታል፡፡
ምርጫው በፌደራል መንግስት ተቀባይነት ስለማግኘቱም እስካሁን የተረጋገጠ ነገር የለም፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሚዋቀረው ጊዜያዊ መንግስት ባለድርሻ የሆኑት የትግራይ ዓለም አቀፍ ምሁራን ሌ/ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤን ለምክትል ፕሬዝዳንትነት እጩ አድረገው ያቀረቡት ባሳለፍነው ሳምንት እንደነበር ይታወሳል፡፡
የትግራይ ሰራዊትም በተመሳሳይ ሌ/ጄነራል ታደሰ ወረደ ለምክትል ፕሬዝዳንትነት መምረጡ አይዘነጋም፡
የአቶ ጌታቸውም ሆነ በምክትል ፕሬዝዳንትነት የተመረጡት ጄነራሎች ሹመት ከፌዴራል መንግስት ጋር በሚደረግው ድርድር የሚጸድቅ ከሆነ እየተንከባለለ ወራት ያስቆጠረው የትግራይ ጊዜያዊ መንግስት የማቋቋም ሂደት ተጠናቆ ወደ ስራ ይገባል ተብሎ ይጠበቃል፡፡