ጥቋቁሮቹ ከዋክብት የተሻለ የማለፍ እድል ያላቸው ሲሆን የማይበገሩት አንበሶች አሸንፈውም የስዊዘርላንድ እና ሰርቢያን ውጤት ይጠባበቃሉ።
የኳታር የአለም ዋንጫ የመጨረሻ የምድብ ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ አፍሪካውያን የሚጠብቋቸው ሁለት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
12 ስአት ላይ ጋና ከኡራጓይ፤ ፖርቹጋል ከደቡብ ኮሪያ ይጫወታሉ።
ከምድብ ሰባት ካሜሮን ከብራዚል፤ ሰዊዘርላንድ ከሰርቢያ ምሽት 4 ስአት ላይ የሚያደርጉት ጨዋታም ተጠባቂ ነው።
አል ጃኑብ ስታዲየም ላይ ኡራጓይን የምትገጥመው ጋና ከአፍሪካ ሁለተኛዋ ጥሎ ማለፉን የተቀላቀለች ሀገር ለመሆን ብርቱ ፍልሚያ ይጠብቃታል።
በ2010 የአለም ዋንጫ ጉዟቸው በልዊስ ስዋሬዝ ሀገር በአሳዛኝ ሁኔታ የተሰናበቱት ጥቋቁሮቹ ከዋክብት ታሪካቸውን ለማደስ ይጫወታሉ።
ከምድቡ ሁለቱንም ጨዋታ ያሸነፈችው ፖርቹጋል አስቀድማ ጥሎ ማለፉን ያረጋገጠች ሲሆን ጋና ሶስት ነጥብ ይዛ ትከተላለች።
ደቡብ ኮሪያ እና ኡራጓይ አንድ ነጥብ ይዘው ወደ ቀጣዩ ዙር ለማለፍ ጋና እና ፖርቹጋልን ይገጥማሉ። ጋና ማሸነፍ አልያም የሁለቱም ጨዋታ በአቻ መጠናቀቅ ወደ ቀጣዩ ዙር ያሳልፋታል።
ከ20 አመት በፊት ፓርቹጋልን ያሸፈችው ደቡብ ኮሪያ ዛሬም ድል ከቀናትና ጋና የምትሸነፍ ከሆነና የጎል ክፍያዋ ከኡራጓይ ከበለጠ ወደ ጥሎ ማለፉ ትገባለች።
የመጀመሪያውን የአለም ዋንጫ ያስተናገደችው ኡራጓይም በኢጁኬሽን ሲቲ ስታዲየም የምታደርገውን ጨዋታ ማሸነፍ እና የጋናን መሸነፍ ትጠብቃለች።
ምሽት 4 ስአት ላይ ደግሞ ካሜሮን የአምስት ጊዜ የአለም ዋንጫ ሻምፒዮኗን ብራዚል በሉሳይል ስታዲየም ትገጥማለች።
ከምድቡ ብራዚል ሁለቱንም የምድብ ጨዋታዎች አሸንፋ ማለፏን ቀድማ አረጋግጣለች።
ዛሬ ሰርቢያን የምትገጥመው ስዊዘርላንድ በሶስት ነጥብ የምትከተል ሲሆን ምሽት ላይ ድል የሚቀናት ከሆነ ጥሎ ማለፉን ትቀላቀላለች።
አንድ ነጥብ የያዘችው ካሜሮን የላቲን አሜሪካዋን ብራዚል ማሸነፍ ብቻ ወደ ቀጣዩ ዙር አያሳልፋትም፤ የስዊዘርንድ እና ሰርቢያ ጨዋታ በአቻ መጠናቀቅ አልያም የሰርቢያን በአንድ የጎል ልዩነት ማሸነፍን ትጠብቃለች።
ካሜሮን እና ብራዚል በ2014ቱ የአለም ዋንጫ ተገናኝተው ሴሌሳዎቹ 4 ለ 1 በሆነ ውጤት ማሸነፋቸው የሚታወስ ነው።