መንግስት፤ በተጀመረው ሕግ የማስከበር ሥራ የታለመው ግብ እየተሳካ ነው አለ
በአማራ ክልል በተሠሩ ሥራዎች ሕዝቡን ለእፎይታ ያበቁ ተግባራት መከናወናቸውም ነው የተገለጸው
በኦሮሚያ ክልል በተከናወነው "አኩሪ ሥራ" በሺዎች የሚቆጠሩ የሸኔ አባላት መገደላቸውን ተረጋግጧል ብሏል
የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤት መንግስት፤ በጀመረው ሕግ የማስከበር ሥራ የታለመውን ግብ እያሳካ እንደሆነ ማረጋገጡን አስታወቀ።
ምክር ቤቱ በወቅታዊ ሀገራዊ የደኅንነትና ጸጥታ ጉዳዮች ዙሪያ ላይ ያደረገውን ምክክር በተመለከተ መግለጫ ሰጥቷል።
በመግለጫው ከአንድ ወር በፊት፣ ሚያዝያ 14 ቀን 2014 ዓ.ም.፣ ሀገራዊ የጸጥታ ሁኔታን በጥልቀት በመገምገም በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት መንግስት የታለመለትን ግብ ያሳካ ጠበቅ ያለ ሕግ የማስከበር ሥራ እየሰራ እንደሆነ ተረጋግጧል ብሏል።
በእርምጃዎቹ ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀምን የመንግሥትን ሕጋዊ ሥልጣን የሚገዳደሩ ኃይሎችንና ሕገ ወጥ ተግባራትን ወደ ተገቢው ሥርዓት የማስገባቱ ሥራ በታቀደለት መንገድና በተሻለ ጥራት እየተከናወነ መሆኑንም ነው ምክር ቤቱ ያስታወቀው።
በኦሮሚያ ክልል በተከናወነው "አኩሪ ሥራ" የሸኔን ልዩ ልዩ ቡድኖች በመደምሰስ፣ ሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎችን በማምከን፣ በጠላት እጅ የነበሩ አካባቢዎችን መልሶ በመቆጣጠር፣ መዋቅሩን በማጥራት፣ ሕዝብን በማወያየትና በማሰለፍ ውጤታማ ሥራ መከናወኑን ለማወቅ ተችሏል እንደ ምክር ቤቱ ገለጻ።
በሺዎች የሚቆጠሩ የሸኔ አባላት መገደላቸውን፣ መማረካቸውንና በፈቃዳቸው እጅ መስጠታቸውን ከሪፖርቶቹ ተረጋግጧል። አያሌ የጦር መሣሪያዎችና ቁሳቁሶች ከሸኔ አባላት ተማርከዋል። መንግሥታዊ መዋቅሩን በሚገባ በማጥራት፣ ለአመራር ብቁ የማድረግ ተግባር በመልካም ሁኔታ ተከናውኗል።
በአማራ ክልል በተሠሩ ሥራዎች ሕዝቡን ለእፎይታ ያበቁ ተግባራት መከናወናቸውንም የብሔራዊ ደኅንነት ምክር ቤቱ ገምግሟል።
በዚህም መሠረት ከጸጥታ ተቋማት የከዱ አባላትን በመያዝ፣ በተለያዩ ወንጀሎች የተሳተፉ አካላትን በቁጥጥር ሥር በማዋል፤ ተበትነው ለጸጥታ ሥጋት ሲሆኑ የቆዩ የጦር መሣሪያዎችን በማሰባሰብ፣ በሕገ ወጥ ተግባር ተሠማርተው የነበሩ አክቲቪስቶችን ሥርዓት በማስያዝ፣ ሕዝቡ የሰላምና የጸጥታው አካል እንዲሆን አወያይቶ በማሰለፍ፣ የተሻለ ሥራ መሠራቱን ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ተመልክቷል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተደረገውን ሰላምና ጸጥታ የማስፈን እንቅስቃሴ ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ በገመገመበት ወቅት አበረታች ሥራዎች መከናወናቸውን ተገንዝቧል። የታጠቁ ሽፍቶችን ሥርዓት ከማስያዝና ከመደምሰስ አንጻር፣ ሕገ ወጥ ተግባትራን ከመቆጣጠር፣ ሕገ ወጥ የጦር መሣሪያዎችን ከመሰብሰብ፣ የተፈናቀሉ ወገኖችን ወደ ቦታቸው ከመመለስ አንጻር የተከናወኑ ተግባራት ለውጥ ያመጡ መሆኑን ለመመልከት መቻሉንም ገልጿል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ በደቡብና በጋምቤላ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥታትም የታጠቁና የተደራጁ ሽፍቶችን መልክ ከማስያዝ፣ የኮንትሮባንድ እንቅስቃሴን ከመግታት፣ በተለያዩ ማኅበረሰቦች መካከል የሚከሠቱ ግጭቶችን ከማስቀረትና ከመፍታት፣ ሕገ ወጥ ተግባራትን ከመቆጣጠር፣ የመንግሥት መዋቅርን ከማጥራት አንጻር ሥራዎቹ በታቀዱት መሠረት መከናወናቸውን አረጋግጧል።
በሶማሌ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥትና በኦሮሚያ አዋሳኝ አካባቢዎች ሊደረግ ታስቦ የነበረው የአልሸባብ እንቅስቃሴ በጸጥታ አካላት ቅንጅት መክሸፉን ብሔራዊ የደኅንነት ምክር ቤቱ ተመልክቷል። አልሸባብ ከጁንታውና ከሸኔ ጋር በተደጋጋሚ ሊያደርጋቸው የሞከራቸው ትሥሥሮች በተጠና የጸጥታ አካላት ኦፕሬሽን እንዲመክኑ መደረጋቸውን ስለማረጋገጡም አስታውቋል ምክር ቤቱ።
ዓለም አቀፍ የሚዲያ ትኩረትን ለመሳብ የሚሞክሩ የጥፋት ኃይሎች በአዲስ አበባ የተለያዩ የጥፋትና ጸጥታን የማደፍረስ እንቅስቃሴዎችን በተደጋጋሚ ሲሞከሩ በተናበበ የጸጥታና ደኅንነት ተቋማቱ አካሄድ እንደከሸፈውም ነው ያስታወቀው።
በዝርፊያና በከተማ ወንጀሎች ላይ ተሠማርተው ነዋሪውን ሲያማርሩ የቆዩ አካላትን ተከታትሎ በሕግ ጥላ ሥር ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራትም ውጤታማ ለውጥ ማምጣታቸውን መመልከቱንም ገልጿል።
ከውጭ የታጠቁ የጸጥታ አደረጃጀቶች እንዳሻቸው እንዲሆኑ መፍቀድ ተገቢ እንዳይደለ ያስታወሰው ምክር ቤቱ በሀገር ውስጥ ኃይልን በብቸኝነት የመጠቀም መብት ያለው መንግሥት ነው ብሏል፤ በሥራው የተሳተፉትን ሁሉ በማመስገን።
"ዜጎች በሰላም ጊዜ አልሚ፣ በጦርነት ጊዜ ተፋላሚ መሆናቸው ከጥንትም የነበረ ነው። ያ ማለት ሀገር ስትወረር ሁሉም ለሀገሩ ተፋላሚ ይሆናል፤ ሀገር ሰላም ስትሆን ደግሞ ሁሉም ወደ ሕጋዊ ማሕቀፍ ይገባል ማለት ነው" ሲልም አስቀምጧል በመግለጫው።
ከዚህ በተጨማሪ በሚዲያ፣ በአክቲቪስትነት፣ በፖለቲካ ቡድን እና በብሔር ስም የሚደረግ "ሀገር የማፍረስ ሤራ"ን መንግሥት በምንም መልኩ እንደማይታገሥ መታወቅ አለበትም ብሏል።
የሃይማኖት ተቋማት በስማቸው "ጥፋት የሚፈጽሙ ነውረኞችን መቆንጠጥ ሲገባቸው ችላ በማለታቸው ጥፋት ፈጻሚዎቹ የልብ ልብ እየተሰማቸውና ተቋማቱን እንደከለላ በመቁጠር" በድርጊታቸው ቀጥለውበታል ያለው ምክር ቤቱ ምእመናንና የሃይማኖት አባቶች የሚገባቸውን ኃላፊነት እንዲወጡ ጠይቋል።
የተጀመረው ሕግና ሥርዓትን የማስከበር ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል በመጠቆምም መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከጸጥታ አካላት ጋር በመሆን የዜግነት ድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርቧል።