ንፁሃንን በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ሲያደርጉ በታዩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ መንግስት ገለጸ
እጅግ አሰቃቂውን ድርጊት የሚያሳይ ተንቀሳቃሽ ምስል በማህበረሰብ ትስስር ገጾች ሲዘዋወር እንደነበር ይታወቃል
ድርጊቱን እጅግ አሰቃቂ እና ከሰብአዊነት ያፈነገጠ ነው ያለው በፈጸሙ
ንፁሃን ዜጎች በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ሲያደርጉ በታዩ አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስድ መንግስት ገለጸ፡፡
“ጽንፈኝነት ሰላምንም ሆነ ፍትህን እዉን ሊያደርግ አይችልም” ሲል መግለጫ ያወጣው መንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሰሞኑን በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ አይሲድ ቀበሌ እጅግ አሰቃቂ እና ከሰብአዊነት ያፈነገጠ ድርጊት ተፈፅሟል ብሏል፡፡
በማህበራዊ ትስስር ገፆች በተንቀሳቃሽ ምስል ሲዘዋወር በቆየው እጅግ አሰቃቂ ድርጊት ንፁሃን ዜጎች በእሳት ተቃጥለው እንዲሞቱ ሲደረግ መታየቱንም ገልጿል።
አገልግሎቱ ድርጊቱ ከኢትዮጵያዊነት ባህል፣ እሴትና ከማንኛውም የሰብዓዊነት እሳቤ ያፈነገጠና እጅግ አሰቃቂ ወንጀል ነው ያለም ሲሆን ይህ እኩይ ድርጊት መጠፋፋትን ያፈጥን ካልሆነ በቀር ሰላምንም ሆነ ፍትህን እዉን ሊያደርግ እንደማይችል ገልጿል፡፡
በመሆኑም ሊኮነንና ሊወገዝ እንደሚገባም ነው የገለጸው፡፡
መነሻቸውም ሆነ ማንነታቸዉ ምንም ይሁን ምን መንግስት ይህን አይነት ፍፁም ከሰብዓዊነት የራቀና ጭካኔ የተሞላበትን ድርጊት የፈፀሙ አካላትን አጣርቶ ህጋዊ እርምጃ ይወስዳል ሲልም አስታውቋል።
በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች የሚታየውን ህገወጥነት ለመቆጣጠርና በንፁሃን ዜጎች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት ለመከላከልም ከክልሉና ከመላው የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን እየተሰራ ይገኛል፤ መንግስት ከዚህ በኋላ የንፁሃን ዜጎችን ህልውና አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላትን አይታገስም ሲል እንዳስታወቀው እንደ አገልግሎቱ ገለጻ።
በመሆኑም በወንጀል ስራ ላይ የተሰማሩና የዜጎችን ህይወት አደጋ ላይ የሚጥሉ አካላት ከወዲሁ ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ በጥብቅ አሳስቧል።
ከአሁን ቀደምም በክልሉ እጅግ አሰቃቂ ወንጀሎች እና የንጹሃን ግድያዎች ተፈጽመዋል፡፡
በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ ከጳጉሜን 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ለተከታታይ ቀናት በተፈጸሙ ጥቃቶች ከ160 በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን አል ዐይን አማርኛ ከአሁን ቀደም መዘገቡም ይታወሳል፡፡