ግጭቶችን ሃይማኖታዊ ገጽታ በማላበስ እንዲባባሱ ለማድረግ የሚሞክሩ ኃይሎችን እንደማይታገስ መንግስት አስታወቀ
ተጠርጣሪዎች ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እየተያዙ መሆኑንም አስታውቋል
ፍትህን በመጠየቅ ሰበብ ህዝበ ሙስሊሙን በክርስቲያን ወንድሞቹ ላይ ለማነሳሳት የሚደረገው ሙከራ ተቀባይነት የሌለው ነውም ብሏል
ከሰሞኑ ያጋጠሙ ግጭቶችን ሃይማኖታዊ ገጽታ በማላበስ እንዲባባሱ ለማድረግ በሚሞክሩ ሃይሎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ መንግስት አስታወቀ፡፡
ግጭቶቹ ሃይማኖታዊ መልክ እንዲይዙና እንዲባባሱ ሙከራ እያደረጉ ያሉ ኃይሎች አሉ ያለው የመንግስት ኮመኒኬሽን አገልግሎት ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ አሳስቧል፡፡
ባሳለፍነው ማክሰኞ ሚያዚያ 18 ቀን 2014 ዓ/ም አራዳ ተብሎ በሚጠራው የጎንደር ከተማ አካባቢ ያጋጠመውን ድርጊት ያወገዘው አገልግሎቱ ሁኔታው እንዳይባባስ ጥረት እየተደረገ እንደሚገኝ ገልጿል፡፡
ግጭቱን ሃይማኖታዊ ሽፋን በመስጠት ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንዲዛመት ለማድረግ ጥረቶች እንደነበሩ የገለጹት የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ለገሰ ቱሉ (ዶ/ር) አብያተ ክርስቲያናትንና የጸሎት ቤቶችን በሌላ በኩል መስጊዶችን የጥቃት ሰለባ የማድረግ አዝማሚያዎች በመታየት ላይ ይገኛሉ ብለዋል፡፡
ይህ "የግጭት ነጋዴዎችና ጽንፈኞች" ድርጊት መሆኑን በመጠቆምም "ፍትህን በመጠየቅ ሰበብ ህዝበ ሙስሊሙን በክርስቲያን ወንድሞቹና እህቶቹ ላይ በማነሳሳት ደም ለማቃባት የሚደረገው ሙከራ ሃገራዊ አንድነትንና ህልውናን ለአደጋ የሚያጋልጥና ለቀውስ የሚዳርግ በመሆኑ በየትኛውም መመዘኛ ተቀባይነት የለውም" ብለዋል፡፡
የእንቅስቃሴው ተሳታፊ አካላት "እኩይ" ካሉት ከዚህ ድርጊት እንዲቆጠቡ እናሳስባለንም ነው ሚኒስትሩ ያሉት፡፡
መንግስት ችግሩ በተፈጠረባቸው አካባቢዎች ከተለያዩ አካላት ጋር በመቀናጀት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር እያዋለ እንደሚገኝም ገልጸዋል፡፡
ግጭቱን ወደተለያዩ አካባቢዎች ለማስፋፋት የሚደረግን የትኛውንም ዐይነት እንቅስቃሴ መንግስት እንደማይታገስም ነው ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ያነሱት፡፡ ህጋዊ እርምጃዎች እየተወሰዱ ይገኛሉም ብለዋል፡፡
ግጭቱን አጸያፊ በሆነ መልኩ ወደ ወራቤ አካባቢ ለማስፋፋት የሚካሄደው የተናበበ የሚመስል እንቅስቃሴ የእስልምናም የክርስትናም አማኞች እንቅስቃሴን እንደማይወክልም ነው ዶ/ር ለገሰ የገለጹት፡፡
ከአሁን ቀደም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ "ታሪካዊ" በሚል የገለጿቸው የኢትዮጵያ ጠላቶች በሃገር ውስጥ ከሚገኙ ተላኪዎቻቸው ጋር በመሆን የከፈቱት "ሃገር የማተራመስ ዘመቻ" ነውም ብለዋል የጥፋት ተልዕኳቸው ሲከሽፍ "የሃይማኖት ካርድ" መምዘዝ መጀመራቸውን በመጠቆም፡፡
ድርጊቱን እናከሽፈዋለን ያሉም ሲሆን ተልዕኮውን ተቀብለው በዚህ እኩይ ተግባር የተሳተፉትን በመልቀም ለህግ ለማቅረብ የተጀመረው ተግባር ተጠናክሮ የሚቀጥል ይሆናልም ብለዋል፡፡ ወንጀልን በወንጀል ለማካካስና ችግሩን ለማወሳሰብ የሚደረግ እንቅቃሴ ከወንጀል ፈጻሚዎች እኩል እንደሚስጠይቅም ነው የተናገሩት፡፡
ሚኒስትሩ በጦርነት የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመገንባት ጥረት በማድረግ ላይ ባለው በአማራ ክልልም ሆነ በአጎራባቾቹ አስተማማኝ ሰላም እንዳይሰፍን፣ ውስጣዊ አንድነት እንዳይኖርና እንዲከፋፈል ህዝቡም እፎይታ እንዳያገኝ ሆን ብለው የሚሰሩ የሽብር ኃይሎች ክልሉንና ሃገሪቱን ወደ አለመረጋጋት እንዲያመሩ እያደረጉ ይገኛሉም ብለዋ በመግለጫቸው፡፡
ይህን አፍራሽ ተልዕኮ በመያዝ ክልሉን የሚያምሱ ጦማሪያን፣ ማህበረሰብ አንቂዎች እና ጽንፈኛ ሚዲያዎች አሉም ነው ያሉት፡፡
እነዚህ ኃይሎች ራሳቸውን እንዲያስተካክሉ የተሰጣቸው እድል ለመጨረሻ ጊዜ እንዲጠቀሙበት እንመክራለንም ብለዋል "በቢላዋ ጠርዝ ላይ ከመጫወት እንዲቆጠቡ" በማሳሰብ፡፡
በጎንደሩ ግጭት እጃቸው እንዳለበት የተጠረጠሩ 280 ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እንዲውሉ መደረጉን የፌደራል የደህንነትና የጸጥታ የጋራ ግብረ ኃይል ትናንት ማስታወቁ ይታወሳል፡፡