ጋዜጠኛ ያየሰው ባለፈው ሳምንት ነበር የዋስትና መብቱ ተከብሮ ከእስር የተፈታው
የኢትዮ ፎረም አዘጋጅ ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ በዋስ ከተፈታ ከሳምንት በኋላ ዛሬ ከቤቱ በደህንነቶች መወሰዱን ጠበቃው አስታወቁ፡፡
ሲቪል የለበሱ ሰዎች ዛሬ ጠዋት አንድ ሰዓት ላይ ያየሰውን ከቤቱ መውሰዳቸውን ጠበቃው ታደለ ገ/መድህን ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡ ጋዜጠኛው ዛሬ ማለዳ ላይ ከመኖሪያ ቤቱ ሲቪል በለበሱ ሰዎች መወሰዱን ጠበቃው ቢገለጹም የት እንደተወሰደ ግን አለመታወቁን ገልጸዋል፡፡
አቶ ታደለ፤ ያየሰው ቀደም ሲል ታስሮበት ወደነበረው የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ማምራታቸውን ቢገልጹም እንደሌለ ተነግሮኛል ብለዋል፡፡ በቀጣይ ወደ ኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ሄደው ሊጠይቁ መሆኑንም ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል፡፡
የአልፋ ቴሌቭዥን የተሰኘ የኦንላይን ሚዳያ መማቋቋም ሲሰራ የነበረው ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረውን በ 10 ሺህ ብር ዋስ ከእስር እንዲፈታ ፍርድ ቤት መፍቀዱ ተገልጿል፡፡
ለጋዜጠኛ በቃሉ የዋስትና መብት የፈቀደው የፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ 2ኛ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት ነው፡፡ ፍርድ ቤቱ፤ የፖሊስ የምርመራ መዝገብን በይደር መርምሮ በዛሬው ቀጠሮ ነው ዋስትና የፈቀደው፡፡
ጋዜጠኛ በቃሉ አላምረውና ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስን ጨምሮ ሌሎች ጋዜጠኞችና የመብት አራማጆች “ሁከትና ብጥብጥ በማስነሳት ወንጀል” ተጠርጥረው በእስር ላይ ናቸው፡፡
የፍትሕ መጽሔት ማኔጅንግ ኤዲተር ጋዜጠኛ ተመስገን ደሳለኝ"ሁከትና ብጥብጥ እንዲነሳ በዩቱብ ኢንተርቪዎችን በመስጠት ቀስቅሷል" በሚል ተጠርጥሮ እስር ላይ ከሚገኙት መካከል አንዱ ሲሆን በአማራ ክልል የሚገኙት የአሻራ ሚዲያና የንስር ሚዲያ ባልደረቦችም
ጋዜጠኛ ያየሰው ሽመልስ ባሳለፍነው ሳምንት በፌደራል የመጀመሪያ ደረጃ ፍ/ቤት አራዳ ምድብ ጊዜ ቀጠሮ ችሎት በሰጠው የዋስትና መብት ከእስር መፈታቱ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት በጋዜጠኞች እና በማህበረሰብ አንቂዎች ላይ እያካሄደ ያለው እስር ትችት አስከትሎበታል፡፡ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ)ም የመንግስት የእስር ድርጊት ኮንኗል፡፡
ነገርግን የኢትዮጵያ መንግስት ተችዎችን እያሰራ አለመሆኑን እና እያካሄደ ያለው ህግ የማስከበር ተግባር መሆኑን በተጋጋሚ እየገለጸ ይገኛል፡፡