በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ መሆኑን መንግስት ገለጸ
ጠቅላይ መምሪያ ዕዙ ስራ መጀመሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል
የአማራ ክልልን ሰላም ለማረጋገጥ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ በሌሎችም አካባቢዎች ተፈጻሚ ይሆናል ተባለ
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ጠቅላይ መምሪያ ዕዝ ሥራ መጀመሩን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
ሚንስትሩ ለገሰ ቱሉ በሰጡት መግለጫ አዋጁ ከታወጀበት ቀን ጀምሮ ከጉዳዩ ጋር ግንኙነት አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች በቁጥጥር ስር እየዋሉ ነው ብለዋል።
በአማራ ክልል የታጠቁ ቡድኖች ለአርሶ አደሩ የግብርና ግብአት በወቅቱና በአግባቡ እንዳይደርስ መንገድ በመዝጋትና ዘረፋ በመፈጸም ሥራዎችን እየተስተጓጎሉ ይገኛሉ ሲሉ ከሰዋል፡፡
ሚንስትሩ በክልሉ ሰላምን እያወከ ነው ያሉት "ቡድኑ" "የመከላከያ ሰራዊት አባላትን ስም በማጥፋትና በመተንኮስ ተግባር ላይ ተሰማርቷል" ብለዋል፡፡
አዋጁ በዋናነት በአማራ ክልል ተግባራዊ እንደሚሆን የተናገሩት ለገሰ ቱሉ፤ የክልሉን ሰላም ለማረጋገጥ ግን አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በሌሎችም አካባቢዎች ተፈጻሚ ይሆናል ብለዋል፡፡
የወጣውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ተግባራዊ በማደረግ ክልሉን ወደነበረበት ሰላም ለመመለስ እንደሚሰራም ተናግረዋል፡፡
በትናንትናው እለት የሚኒስትሮች ምክርቤት በአማራ ክልል መደበኛ በሆነው የህግ ማስከበር መቆጣጠር አለመቻሉን እና አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጁ መወሰኑን ማስታወቁ ይታወሳል።
የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ለስድስት ወራት ጸንቶ ይቆያል።
በአማራ ክልል ባለፈው ሚያዚያ ወር የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ኃይሎች እንዲፈርሱ መወሰኑን ተከትሎ የአማራ ልዩ ኃይል አይፈርስም የሚል ተቃውሞ በክልል ተካሂዶ ነበር። ይህን ተከትሎ በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተባብሶ ቀጥሏል።