መንግስት አቶ ታየ “በሽብር ተግባራት በተለይም ደግሞ ከእገታ ጋር በተያያዘ እጁ እንዳለበት ደርሼበታለሁ” ብሏል
የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት አቶ ታየ ደንደአ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን መንግስት አስታወቀ።
አቶ ታየ ደንደዓ ከሰሞኑ በመንግስት እና በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት መካከል ሲደረግ ስለነበረው ድርድር ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት አስተያየት መንግስታቸውን ተጠያቂ ማድረጋቸው ይታወሳል።
በአዲስ አበባ ሊካሄድ የነበረው "የጦርነት ይቁም" ሰላማዊ ሰልፍ መከልከሉ ተገቢ አለመሆኑንም በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ማስፈራቸው አይዘነጋም።
አቶ ታየ ደንደአ በትናትናው እለት ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በተጻፈ ደብዳቤ ከሀላፊነታቸው እንደተነሱ መነገሩ ይታወቃል።
አቶ ታየ ይንንን ተከትሎ በማሀበራዊ ትስስር ገጻቸው “የወንድማማቾች መገዳደል ይቆም ዘንድ ለሰላም በመወገኔ ከስልጣን አነሱኝ” ብለው ነበር።
የፀጥታና ደህንነት የጋራ ግብረ ኃይል ባወጣው መግለጫ፤ የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ የነበሩት ታየ ደንደአ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አስታውቋል።
ግብረ ኃይሉ በመግለጫው አቶ ታየ ደንደአ፤ "በመንግስት ቁጥጥር ስር ሊዉል እንደሚችል ሲገምት ታጋይ ለመምሰል በራሱና በተለያዩ የማህበራዊ ሚዲያ ትስስር ገጾች አፍራሽና ፀረ ሰላም ፅሁፎችን፣ ንግግሮችንና መግላጫዎችን በማን አለብኝነት ሲያስተላልፍና ሲሰጥ ቢቆይም ከተጠያቂነት ማምለጥ ባለመቻሉ በጋራ ግብረ ኃይሉ በቁጥጥር ስር ውሏል" ብሏል።
አቶ ታየ "የሰላም ሚኒስትር ዴኤታ ሆኖ ሰላምን ለማስፈን መሥራት ሲገባዉ፤ በተቃራኒዉ ኢትዮጵያን ለማፍረስ ከሚንቀሳቀሱ ፀረሰላም ኃይሎች ጋር በመተሳሰር ለጥፋት ተልዕኮ በህቡዕ ሲሰራ ተደርሶበታል” ም ነው ያለው ግብረሃይሉ በመግለጫው።
“በተለያዩ አካባቢዎች በንፁሃን ዜጎች ላይ ሲፈፀሙ በነበሩ የሽብር ተግባራት በተለይም ደግሞ ከእገታ ጋር በተያያዘ እጁ እንዳለበት ተደርሶበታል” ሲል አስታውቋል።
በተጨማሪም፤ “አቶ ታየ ደንደአ መንግስታዊ ኃላፊነቱን ተቀብሎ እየሰራ በነበረበት ወቅት መንግስታዊና የፓርቲ መዋቅሩን በሴራ ለመናድ በህቡእ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን በመረዳት ያላሰለሰ ጥናትና ክትትል ሲደረግበት ነበር” ብሏል።
በተደረገው ክትትልም አቶ ታየ ደንደአ ከኦነግ ሸኔ አመራሮችና በሽብር ወንጀል ከተጠረጠሩ ጽንፈኛ ኃይሎች ጋር ትስስር በመፍጠር መንግስትን በአመጽ፣ በሽብርና፣ በትጥቅ ትግል ለመጣል ሲያሴር እንደተደረሰበት መግለጫዉ ጠቁሟል።
ግብረ ኃይሉ በመግለጫው በማከልም፤ በመንግስትና በፖርቲ መዋቅር ዉስጥ ሆነዉ በተመሳሳይ እኩይ ዓላማ በተሰማሩ አካላት ላይ በጥናት የተመሰረተ ጥብቅ ክትትል እያደረገባቸዉ እንደሚገኝና እንደአስፈላጊነቱ የሚወሰዱ ህጋዊ እርምጃዎችን በተከታታይ ለህዝብ ይፋ እንደሚያደርግ አስታዉቋል።