የመንግስት ጦር የህወሓትን እንቅስቃሴ ለመግታት የወልዲያ-መቀሌ አውራ ጎዳናን መቆጣጠሩን አስታወቀ
ወታደራዊ ጠቀሜታ እንዳላቸው የተገለጹት የዞብል ተራሮች በመንግስት ጦር ተይዘዋል ተብሏል
ዘመቻው በሜካናይዝድ እና በአየር ኃይል ተመራ እንደሆነም መንግስት አስታውቋል
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የሚመራው የኢትዮጵያ ጥምር ጦር የወልዲያ መቀሌ አውራ ጎዳና መቆጣጠሩን አስታወቀ፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት እንዳለው በጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመሩት የጸጥታ ኃይሎች ጥምረት፣በህወሃት ላይ ማጥቃት መሰንዘራቸውን ገልጾ፤ በምሥራቅ ግንባር ስትራቴጂያዊ የሆኑትን የዞብል ሠንሠለታማ ተራሮችን ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን የአርጆ፣ ፎኪሳ እና ቦረን ከተሞችን መቆፃፀሩን ገልጿል፡፡
መንግስት በተመሳሳይ ሁኔታ የጉራ ወርቄ አካባቢዎችን መቆጣጠሩ ገልጾ፤ የወልድያ መቀሌ ዋናውን አውራ ጎዳና መቁረጡንም አስታውቋል፡፡ በዚሁ ግንባር የድሬ ሮቃና የሶዶማ ከፍተኛ ወታደራዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ከተሞችና ተራሮች የተቆጣጠረው ጥምር ጦሩ አሁን ወደ ሐራ ከተማ እየገሠገሠ ነው ብሏል፡፡
ጥምር ጦሩ፤ በውጫሌ ግንባር የአምባሰል ከፍተኛ ሠንሠለታማ ተራሮችን ጨምሮ የሮቢትና የጎልቦን፣ በወረባቦ ወረዳ የሚሌ ኮትቻን፣ በሐብሩ ወረዳ የኮልቦን፣ የመርካታና የፋጂን አካባቢዎችን መቆጣጠሩንና አሁን ላይ ወደ መርሳ ከተማ እያቀነ እንደሆነ አስታውቋል፡፡
በእነዚህ ግንባሮች በተደረገው ኦፐሬሽን የህወሃት ሃይል በተሰነዘረበት ማጥቃት ሙት፣ ቁስለኛና ምርኮኛ መሆኑን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል፡፡ ይህንን ዘመቻ የደረጉት የመካናይዝድ ኃይል እና የአየር ኃይል በጥምረት መሆኑ የተገለጸ ሲሆን በዚህም ህወሃት ምንም ዓይነት ተሸከርካሪ እና ከባድ መሣሪያዎችን ይዞ እንዳይንቀሳቀስ ተደርጓል ተብሏል፡፡
በዚህ ኦፕሬሽን ህወሃት ለበርካታ ቀናት ያከማቻቸውን ቁስለኞችን እና ከተለያዩ ቦታዎች የተዘረፉ ንብረቶችን ትቷቸው መሄዱን መንግስት ገልጿል፡፡
ህወሃት ዋናው የቆቦ ወልድያ መንገድ ስለተዘጋበት በጋሸና ላሊበላ በኩል ለማምለጥ ከፍተኛ ትንቅንቅ ቢያደርግም በጥምር ጦሩ እንደከሸፈበት ተገልጿል፡፡
በፌደራል መንግስትና በህወሃት ሃይሎች መካከል ያለው አለመግባባት ወደ ወታደራዊ ግጭት ከገባ ከ8 ወራት በኋላ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፤ጦሩን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱ ይታወሳል፡፡
ነገርግን በኢትዮጵያ መንግስት በሽብር የተፈረጀው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ጥቃት መክፈቱንና ይህንም ለመቀልበስ እንደሚንቀሳቀስ መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ውስጥ በመንግስት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት እየተካሄ የሚገኝ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ከግንባር ሆነው ባስተላለፉት መልእክት፤ ጦርነቱን መንግስት ማሸነፉ የማይቀር ስለሆነ የህወሓት ታጣቂዎች እጃቸውን ለጸጥታ አካላት እንዲሰጡ ጥሩ በትናንትናው እለት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡