መንግስት በህወሓት ተይዘው የነበሩትን ደሴና ከምቦልቻ ከተሞችን ነጻ ማውጣቱን አስታወቀ
መንግስት በቅርቡ ታሪካዊቷን ላሊበላ ከተማን ነጻ ማውጣቱን ይታወሳል
መንግስት ከደሴና ከምቦልቻ በተጨማሪ ባቲን፣ቀርሳን፣ ገርባንና ደጋንንና ቃሉ ወረዳን ነጻ ማውጣቱን አስታውቋል
መንግስት በህወሓት ተይዘው የነበሩት ሁለት ትላልቅ ከተሞች---ደሴና ከምቦልቻን ህወሓትን በማስለቀቅ መልሶ መያዙን የመንግስት ኮሙኒኬሽን አስታውቋል፡፡
መንግስት እንደገለጸው ከደሴና ኮምቦልቻ በተጨማሪ በምሥራቅ ግንባር ባቲን፣ቀርሳን፣ ገርባንና ደጋንን ነጻ ያወጣ ሲሆን በሐርቡ ግንባር ደግሞ ቃሉ ወረዳን ሙሉ በሙሉ መቆጣጠሩን አስታውቋል፡፡
- “ከእንግዲህ እኔ መከላከያን በግንባር ሆኜ ለመምራት ከነገ ጅምሮ ወደ ትግሉ ሜዳ እዘምታለሁ”- ጠ/ሚ ዐቢይ
- ለህወሓት የተሰለፉ ሁሉ እጃቸውን እንዲሰጡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ጥሪ አቀረቡ
- የላሊበላ ከተማ በመንግሥት የጸጥታ አካላት ቁጥጥር ስር መዋሏን መንግስት አስታወቀ
መንግስት በተለይም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወደ ግንባር ከዘመቱ በኃላ በአማራ እና አፋር ክልሎች በርካታ ከተሞችን ከህወሃት አስለቅቋል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን አገልግሎች ዛሬ በሰጠው መግለጫ ህወሓት በአማራና አፋር ክልሎች የዘር ማጥፋት ወንጀል መፈጸሙን መግለጹ ይታወሳል፡፡
የአገልግሎቱ ሚኒስትር ዴኤታ ሰላማዊት ካሳ በሰጡት መግለጫ በማይካድራ፣ በጭና፣ በጋሊኮማ፣ በአጋምሳ፤ቆቦ፣ ውርጉሳ፣ ውጫሌ ከምቦልቻና እና በሌሎችም አካባቢዎች ተመሳሳይ ወንጀሎችን የፈጸመው ቡድኑ በንጹሃን ላይ የጅምላ ጭፍጨፋ መፈጸሙን ገልጸዋል፡፡
ሚኒስትር ዴኤታዋ ወንጀሉ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ እና ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጭምር እንዲያውቀው ይደረጋል፤ የመንግስትም ስራው ይሄው ነው ብለዋል፡፡
ሌሎች ዓለም አቀፍ ተቋማትም ይህንኑ እንደሚያደርጉ ይጠበቃል ብለዋል ሚኒስትር ዴኤታዋ፡፡
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮሚሽን(ኢሰመኮ) በትግራይ ክልል እንደተደረገው ሁሉ በአማራና አፋር ክልሎች ተመድን ያሳተፈ የሰብአዊ መብት ጥሰት ምርመራ ሊካሄድ እንደሚችል የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በቅርቡ ለአል ዐይን አማርኛ መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
በፌደራል መንግስትና በህወሃት ሃይሎች መካከል ያለው አለመግባባት ወደ ወታደራዊ ግጭት ከገባ ከ8 ወራት በኋላ ሰኔ 21 ቀን 2013 ዓ.ም መንግስት የተናጠል ተኩስ አቁም አውጆ፤ጦሩን ከትግራይ ክልል ማስወጣቱ ይታወሳል፡፡
ነገርግን በኢትዮጵያ መንግስት በሽብር የተፈረጀው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ጥቃት መክፈቱንና ይህንም ለመቀልበስ እንደሚንቀሳቀስ መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ውስጥ በመንግስት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት እየተካሄ የሚገኝ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ከግንባር ሆነው ባስተላለፉት መልእክት፤ ጦርነቱን መንግስት ማሸነፉ የማይቀር ስለሆነ የህወሓት ታጣቂዎች እጃቸውን ለጸጥታ አካላት እንዲሰጡ ጥሩ በትናንትናው እለት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡