የላሊበላ ከተማ በመንግሥት የጸጥታ አካላት ቁጥጥር ስር መዋሏን መንግስት አስታወቀ
ጋሸናን ጨምሮ በርካታ ስፍራዎች ዛሬ ከህወሓት ነጻ መውጣታቸው ይታወቃል
የሰቆጣ ከተማን ለመቆጣጠር ወደፊት እየገሠገሡ መሆኑንም መንግስት አስታውቋል
የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ ታሪካዊቷን የላስታ ላሊበላ ከተማንና የላሊበላ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን መቆጣጠራቸውን መንግስት አስታወቀ።
በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ውቅር አብያተ ክርስቲያናት የሚገኙባትን የላሊበላ ከተማንና ዓለም አቀፍ የአውሮፕላን ማረፊያውን ለመቆጣጠር የተቻለው ጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት በየግንባሩ የተጀመረው ማጥቃት ውጤት ማስመዝገብ በመቻሉ እንደሆነ የመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት አስታውቋል።
- የህወሓት ኃይሎች ላሊበላን ከተቆጣጠሩ በኋላ በት/ቤቶች ካምፕ ሰርተው መቀመጣቸውን ነዋሪዎች ገለጹ
- የላሊበላ ፍልፍል አብያተ ክርስቲያናት ጉዳይ በጽኑ እንደሚያሳስበው ዩኔስኮ አስታወቀ
የመከላከያ ሠራዊት፣ የአማራ ልዩ ኃይል፣ ሚሊሻና ፋኖ የላስታ ላሊበላን አካባቢ በማጽዳት የሰቆጣ ከተማን ለመቆጣጠር ወደፊት እየገሠገሡ መሆኑንም ገልጿል።
በወረራ ሥር የሚገኙ የዋግ ሕምራ፣ የሰሜንና የደቡብ ወሎ ሕዝብ፣ ከመንግሥት የጸጥታ አካላት ጋር በመሆን ነጻነቱን እንዲያስከብር መንግሥት ጥሪ ማቅረቡንም ከመንግስት ኮሚኒኬሽን አገልግሎት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በኢትዮጵያ መንግስት በሽብር የተፈረጀው ህወሃት በአማራና አፋር ክልሎች ጥቃት መክፈቱንና ይህንም ለመቀልበስ እንደሚንቀሳቀስ መንግስት መግለጹ ይታወሳል፡፡
በአሁኑ ወቅት በአማራ ክልል ውስጥ በመንግስት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ጦርነት እየተካሄደ የሚገኝ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ወደ ጦር ግንባር ዘምተዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ከግንባር ሆነው ባስተላለፉት መልእክት፤ ጦርነቱን መንግስት ማሸነፉ የማይቀር ስለሆነ የህወሓት ታጣቂዎች እጃቸውን ለጸጥታ አካላት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡