ለኢትዮጵያ ልብ ማእከል ድጋፍ የሚደረግበት የሩጫ ውድድር በዋሽንግተን ዲሲ ሊካሄድ ነው
ሩጫው በመጪው ጥቅምት 6 ቀን 2014 ዓ.ም እንደሚካሄድም ነው አዘጋጆቹ ያስታወቁት
ውድድሩ በታላቁ አፍሪካ ሩጫ አዘጋጅነት ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን ደራርቱን ጨምሮ ታዋቂ አትሌቶች ይገኙበታል ተብሏል
ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማእከል ድጋፍ የሚደረግበት የሩጫ ውድድር በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ሊካሄድ ነው፡፡
ውድድሩ በመጪው ጥቅምት 6 ቀን 2014 ዓ.ም (ኦክቶበር 16፣ 2021) ነው የሚካሄደው፡፡
በታላቁ አፍሪካ ሩጫ (Grand African Run) አዘጋጅነት ለ3ኛ ጊዜ የሚካሄድ ሲሆን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌደሬሽን ኘሬዝዳንት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉን ጨምሮ ሌሎች ታዋቂ ሰዎች እንደሚሳተፉበት አዘጋጆቹ ለአል ዐይን አማርኛ በላኩት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡
ሌሎች ከ20 በላይ ኦሎምፒያኖች፣ የዓለም ሻምፒዮኖች እና የአገር ባለውለታዎች በውድድሩ ላይ በክብር እንግድነት እንደሚሳተፉም ነው የገለጹት፡፡
ባለፉት ስልሳ አመታት ኢትዮጵያዊ አትሌቶች የሀገራቸውን መልካም ገፅታ በማስተዋወቅ በኩል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውን የተናገረችው ኮማንደር ደራርቱ “ውድድሩን እንደ መልካም አጋጣሚ መድረክ በመጠቀም በዉጭ የሚኖሩ ወገኖቻችንን ግንኙነት ማጠናከር እና የባህል ልውውጥ ማድረግ ያስፈልጋል” ብላለች።
ትዕግስት ገዛኸኝ ለኢትዮጵያ የመጀመሪያውን የፓራሊምፒክ ወርቅ አስገኘች
ዝግጅቱ “ማህበረሰባችን የተለየ ቦታ የሚሰጠውን የአትሌቲክስ ስፖርት በመጠቀም አብሮነትን ለማጎልበት” እንደሚያስችልም ገልጻለች።
ታላቁ የአፍሪካ ሩጫ በዲሲ እንደገለጸው አርቲስት መሰረት መብራቴን የበጎ ፈቃድ አምባሳደር ላደረገው ለኢትዮጵያ የልብ ህሙማን ህፃናት መርጃ ማእከል ድጋፍ ያደርጋል::
አርቲስት መሰረት ለዚሁ በጎ አላማ በተለያዩ የአሜሪካ ግዛቶች የገቢ ማሰባሰቢያ መርሃ ግብሮችን እያከናወነች እንደሆነ ይታወቃል፡፡
ውድድሩ “አብሮነት መሻል ነው” በሚል መሪ ቃል እንደሚካሄድ የተናገሩት የታላቁ የአፍሪካ ሩጫ በዲሲ ዋና አዘጋጅ ዶ/ር ጋሻው አብዛ፤ ዝግጅቱ ከአንድ ቀን የ5 ኪ.ሜ የቤተሰብ ሩጫነት የበለጠ ፋይዳ ያለው መርሀግብር መሆኑን ጠቁመዉ፤ ኢትዮጵያዊያንና ትውልደ ኢትዮጵያንን በማቀራርብ ረገድ ጉልህ ሚና እንዳለው ገልፀዋል።
“ኢትዮጵያዊያንን በአንድነት ማሰባሰብን፣ ማስተዋወቅን እና የበለጠ ማቀራረብን እግረ መንገድንም ለተለያዩ የበጎ አድራጎት ስራዎች ገቢ ማሰባሰብን ዓላማው አድርጎ የሚካሄድ ነው”ም ነው ዶ/ር ጋሻው ያሉት።
በውድድሩ በሺዎች የሚቆጠሩ የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማህበረሰብ አባላት እንደሚሳተፉም ገልጸዋል፤ አሁንም በውድድሩ መሳተፍ የሚፈልጉ በአዘጋጆቹ ዌብሳይት በኦንላየን www.africanrun.com ለመመዝገብ እንደሚችሉ በመጠቆም።
ለሶስት ወራት የትርዒት ጉዞ ወደ አውሮፓ ያቀናው ሰርከስ ደብረብርሃን
ከአሁን ቀደም በተካሄዱት ሁለት የታላቁ አፍሪካ ሩጫ ውድድሮች ኮማንደር ደራርቱን እና የዲባባ ቤተሰብ አባላትን ጨምሮ ቀነኒሳ በቀለን፣ ሚሊዮን ወልዴ፣ ፋጡማ ሮባ እና ሌሎችንም መሰል ታላላቅ ኢትዮጵያውያን አትሌቶች በክብር እንግድነት መገኘታቸውን አዘጋጆቹ ገልጸዋል፡፡