የጊኒ ጁንታ የጠቅላይ ሚኒስትርነት ስፍራን ለሲቪል አመራር ሰጠ
የቀድሞ የመንግስት ሰራተኛ የነበሩት መሃመድ ቤቮጊን የጊኒ ጠቅላይ ሚኒስትር ተገርገው ተሹመዋል
የጊኒ መፈንቅለ መንግስት መሪ ኮሎኔል ማማዲ ዱምቦያ የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት በመሆን ቃለ መኃላ መፈጸማቸው ይታወሳል
የጊኒ ወታደራዊ ጁንታ የቀድሞ የመንግስት ሰራተኛ የነበሩትን መሃመድ ቤቮጊን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ ሾመ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው የተሸሙት መሃመድ ቤቮጊን ከዚህ ቀደም የግብርና ፋይናንስ ባለሙያ ሆነው ሲሰሩ መቆየታቸው ተሰምቷል።
የጊኒ ጁንታ ከዚህ ቀደም የሲቪል ሰራተኛ የነበሩትን መሃመድ ቤቮጊን ጠቅላይ ሚኒስትር አድርጎ የሾመው ስልጣኑን ወደ ዴሞክራሲያዊ የሲቪል አስተዳደር ለመመለስ የገባውን ቃል ለማረጋገጥ እንደሆነም ተነግሯል።
አዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሃመድ ቤኖቪ የጊኒ ታዋቂው ዲፕሎማት ዲያሎ ቴሊ የቅርብ ዘመድ መሆናው ታውቋል።
ዲፕሎማቱ ዲያሎ ቴሊ የቀድሞው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የመጀመሪያው ሊቀ መንበር እንደነበሩ የሚታወስ ሲሆን፤ በአምባገነኑ ስኩ ቱሬ ዘመነ መንግስት በ1977 መገደላቸው ይታወሳል።
የአዲሱ ጠቅላይ ሚኒስትር መሃመድ ቤኖቪ ሹመትም በቴሌቪዥን በተላለፈ መግለጫ ለህዝብ እንዲታወቅ መደረጉን ሮይተርስ ዘግቧል።
የቀድሞ የጊኒ ፐሬዚዳንትን በመፈንቅለ መንግስት ያነሳው የወታደራዊ ጁንታ መሪ ኮሎኔል ማማዲ ዱምቦያ የሀገሪቱ ጊዜያዊ ፕሬዝዳንት በመሆን ቃለ መኃላ መፈጸማቸው ይታወሳል።
አዲሱ ፕሬዝዳንት ማማዲ ዶምቦያ በመፈንቅለ መንግስት ያስወገድዋቸው የ83 ዓመት አዛውንቱ የቀድሞው ፕሬዝዳንት አልፋ ኮንዴን በተመለከተ “ደህንነቱ በተጠበቀ ቦታ” ላይ ይገኛሉ ከማለት በዘለለ ያሉበት ቦታ የት እንደሆነ ከመናገር ተቆጥበዋል።