የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝበ ውሳኔ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲካሄድ መወሰኑን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስታወቀ
የምርጫ ቦርድ የኮሙኒኬሽን አማካሪ ሶሊያና ሽመልስ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ቦርዱ፤ ሕዝበ ውሳኔው ከምርጫው ጎን ለጎን ሰኔ 14 ይካሄዳል ቢባልም በመጨረሻ ግን ጳጉሜ 1 ቀን 2013 እንዲካሄድ መወሰኑን ይፋ አድርገዋል፡፡
ሕዝበ ውሳኔ የሚደረግባቸው አካባቢዎች አስተዳደሮች ማለትም የከፋ፣ ዳውሮ፣ ቤንች ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞና የሸካ ዞኖች እንዲሁም የኮንታ ልዩ ወረዳ አስተዳደሮች ሕዝበ ውሳኔው ከምርጫው ጋር አብሮ አለመደረጉን በተመለከተ ተቃውሞ አቅርበው እንደነበር ይታወሳል፡፡
ዞኖች ቅሬታ አቅርበው እንደነበር ያነሱት ወ/ት ሶሊያና፤ ብዙ ከመራጮች ምዝገባ ጋር ተያይዞ የተነሱትን ጥያቄዎችን ለመፍታት ጊዜ ስለሚያስፈልግ ምርጫውን እና የሕዝበ ውሳኔውን የግድ ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም እንዲደረግ ተወስኗል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድም ከአካባቢዎቹ አመራሮች ጋር ውይይት አድርጎ ነበር፡፡ አምስቱ ዞኖች እና አንድ ልዩ በአንድ ክልል ስር ለመደራጀት ያቀረቡት ጥያቄ ሰኔ 14 በሚካሄድ ሕዝበ ውሳኔ ምላሽ ያገኛል ተብሎ የነበረ ቢሆንም፤ ቦርዱ አሁን እየሰጠ ባለው መግለጫ ሕዝበ ውሳኔው ጳጉሜ 1 ቀን 2013 ዓ.ም ይካሄዳል ብሏል፡፡
በዚሁ ዕለት በሚደረግ ሕዝበ ውሳኔ ይዋቀራል ተብሎ ለሚጠበቀው “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል” ሕገ መንግስት እየተዘጋጀለት መሆኑን የደቡብ ምዕራብ ሕዝቦች ሕዝበ ውሳኔ ማስፈጸሚያ ፕሮጄክት ጽ/ቤት ለአል ዐይን አማርኛ መግለጹ ይታወሳል፡፡ የፕሮጀክት ጽ/ቤቱ ስራ አስኪያጅ ምትኩ በድሩ (ኢ/ር)፣ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ አዲስ ይዋቀራል ተብሎ ለሚጠበቀው ክልል የሰነድ ስራዎች እየተዘጁለት መሆኑን መግለጻቸው ይታወሳል፡፡
ምንም እንኳን የሕዝበ ውሳኔው ውጤትና አጠቃላይ ዝግጅቱ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የሚመራና የሚገለጽ ቢሆንም በሕዝበ ውሳኔው ውጤት ክልሉ የሚመሰረት ከሆነ በሚል ዝግጅቶች እየተደረጉ መሆኑንም ስራ አስኪያጁ ተናረው ነበር፡፡
የክልል ስያሜ ፣ ሰንደቅ ዓላማ ፣ የሥራ ቋንቋና ሌሎችም ጉዳዮች የሚካተቱበት ሕገ መንግስት እየተዘጋጀ እንደሆነም ተገልጿል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝበ ውሳኔ የምርጫ ምልክትን ቀደም ብሎ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል፡፡ በዚህም የተያያዙ እጆች የኮንታ ልዩ ወረዳ፣ የምዕራብ ኦሞ ዞን፣ የቤንች ሸኮ ዞን፣ የካፋ ዞን፣ ዳውሮ ዞን እና የሸካ ዞን ከደቡብ ብሔር፣ ብሔረሰቦች እና ህዝቦች ክልል ወጥተው የጋራ አንድ ክልል መመስረታቸውን እደግፋለሁ የሚለውን እንደሚወክል መገለጹ ይታወሳል፡፡