የኢትዮጵያ መንግስት፤የአፋር እና የትግራይ ባለስልጣናት በቅርቡ ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች ምግብ እንዲደርስ የወሰዱትን እርምጃ አሜሪካ ታበረታታለች ብሏል መግለጫው
የኢትዮጵያ መንግስት በትግራይ መሰረታዊ አገልግሎቶችን እንዲመልስ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ ጠይቋል፡፡
በኢትዮጵያ መንግስት እና በህወሓት መካከል የተኩስ አቁም ስምምነት እንዲደረስ፣አስፈላጊ የሆነ የጸጥታ አሬንጅመንት (ማመቻቸት) እንዲደረግ እና መሰረተ ልማቶች በአስቸኳይ እንዲመለሱ ጠይቋል፡፡ አሜሪካ በኢትዮጵያ የተፈጠረው የፖለቲካ ችግር መፍትሄ እንዲያገኝ እና በሀገሪቱ ያለው ክፍፍል ተቀርፎ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰላም እንዲሰፍን በቁርጠኝነት ትስራለች ብሏል መግለጫው፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት፤የአፋር እና የትግራይ ባለስልጣናት በቅርቡ በጦርነት ምክንያት ችግር ላይ ለወደቁ ሰዎች አስፈላጊ የሆነ ምግብ እንዲደስ የወሰዱትን እርምጃ አሜሪካ ታበረታታለች ብሏል መግለጫው፡፡
የአሜሪካ መንግስት፣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ መንግስት እስረኞችን መልቀቁ እና የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ማንሳቱ እና የትግራይ ሃይሎችም ግጭት ማቆማቸውን በበጎ እንደምታየው ገልጻለች፡፡
የትግራይ ኃይሎች ከአብዛኛው የአፍር ክልል መውጣታቸው እና ለሰላማዊ መፍትሄ ቁርጠኛ መሆናቸውን መግለጻቸውን አሜሪካ እንደምታበረታታ መግለጫው ጠቅሷል፡፡
ህወሓት ከአፋር ክልል ሙሉበሙሉ መውጣቱን የገለጸ ቢሆንም የአፋር ክልል መንግስት እና የፌደራል መንግስት አፋር ክልል ሙሉ በሙሉ አልወጣም ብለዋል፡፡
“አሸባሪው ህወሀት በከባድ መሳሪያ በመታገዝ ከወረራቸው በአፋር ክልል የኪልበቲ ረሱ ዞን ወረዳዎች ሙሉ በሙሉ ወጥቻለሁ በማለት ከሰሞኑ ከእውነት የራቀ የሀሰት የማደናገሪያ ፕሮፖጋንዳ በማሰራጨት ላይ ይገኛል።” ብሏል የአፋር ክልል መንግስት በቅርቡ በሰጠው መግለጫ፡፡
ርሃብ ውስጥ ላለችው ትግራይ ምግብ እንዲሰርስ በማሰብ፣የህወሓት ሃይሎች ከጎረቤት አፋር ክልል ሙሉ በሙሉ መውጣታቸውን ሮይተርስ የህወሓትን ቃል አቀባይ አቶ ጌታቸው ረዳን ጠቅሶ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
የመንግስት ኮሙኒኬሽን ሚኒስቴር ትናንት በሰጠው መግለጫ ወራሪው የትግራይ ኃይል አሁንም የእርዳታ አቅርቦቱ የተሳለጠ እንዳይሆን እያረገ ነው ብሏል፡፡
ሚኒስትሩ ለገሰ ቱሉ ወደ ትግራይ የእርዳታ እህል ጭነው ከገቡት 1999 የከባድ የጭነት ማመላለሻ ተሽከርካሪዎች አልመለሱም፤ ግጭት ከማቆም ውሳኔው በኋላም እርዳታ ጭነው ከሄዱት 145 መካከል እስካሁን የተመለሱት ከ40 በታች ብለዋል፡፡
ከአማራ እና ከአፍር የወሰን አካባባዎች የተወሰኑትን ብቻ በመልቀቅ እና ገዥ መሬቶችን በመያዝ ከአፋር ክልል የወጣ በማስመሰል አለም አቀፉን ማህበረሰብ ለማሳሳት የሃሰት ፕሮፓጋንዳ እየሰራ ነው ብለዋል፡፡
ሚኒስትሩ አለምአቀፉ ማህበረሰብ ከያዛቸው የአፋር እና የአማራ አካባቢዎች እንዲወጣ እና እርዳታ ጭነው ወደ ትግራይ የሄዱ ተሽካርካሪዎች እንዲመልስ ጫና እንዲያሳድር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
በፌደራል መንግስት እና በህወሓት ኃይሎች መካከል ያለው ግጭት በሰላም እንዲፈታ በአሜሪካ የሚደገፍና በአፍሪካ ህብረት አማካኝነት የሚመራ ንግግር ከተጀመረ ወራቶች አልፈዋል፡፡
ከቀሰቀሰው ግጭት ከ18 ወራት ባላይ የሆነው ግጭት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ህይወታቸውን እንዲያጡ እና በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች እንዲፈናቀሉ እና ህይወታቸው እንዲጎሳቆል አድርጓል፡፡