ሙሳ ፋኪ መሃመት፣ በትግራይ ክልል እየተዋጉ ያሉ አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ አሳሰቡ
መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ወደ ተጠራው የሰላም ድርድር እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል
በሰሜን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ ያገረሸው ጦርነት ስጋት እንደፈጠረባቸው ኮሚሽነሩ አስታውቀዋል
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃመት በትግራይ ክልል እየተዋጉ ያሉ አካላት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ አቁም እንዲያደርጉ አሳሰቡ።
ሙሳ ፋኪ መሃመት በሰሜን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ ያገረሸውን ጦርነት አስመልክቶ በዛሬው እለት መግለጫ አውጥተዋል
ሊቀ መንበሩ በመግለጫቸው፣ በሰሜን ኢትዮጵያ እንደ አዲስ የተቀሰቀሰውን ጦርነት እየተከታተሉት መሆኑን እና ከፍተኛ ስጋት እንዳሳደረባቸው አስታውቀዋል።
እየተዋጉ ያሉ አካላት ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ የተኩስ ኡም እንዲያደርጉ ያሳሰቡት ሙሳ ፋኪ መሃመት፣ የሰብዓዊ አገልግሎቶች ወደ ነበሩበት አንዲመለሱም ጥሪ አቅርበዋል።
መንግስት እና ህወሓት በአፍሪካ ቀንድ ከፍተኛ ተወካይ በሚመራው እና በዓለም አቀፉ መህበረሰብ በሚደገፈው በደቡብ አፍሪካ ወደ ተጠራው የሰላም ድርድር እንዲመጡም ጥሪ አቅርበዋል።
ከተጀመረ ሁለት ዓመት የሞላው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ለወራት ቆሞ የነበረ ሲሆን፣ ባለፈው ነሐሴ 18/2014 ዓ.ም ድጋሚ መቀስቀሱ ይታወሳል።
ጦርነቱን እንደ አዲስ በመጀመር መንግስት እና ህወሓት እርስ በእርስ ሲካሰሱ ይስተዋላል። ያም ሆኖ ሁለቱም አካላት የተደጀመረውን ሰላም ንግግር ጥረት እንዲቀጥል ዝግጁ መሆናቸው ሲገልጹ ይደመጣሉ።
የኢትዮጵያ መንግስት በድጋሚ ጦርነት ከመቀስቀሱ በፊት ያለምንም ቅድመ ሁኔታ በየትኛው ቦታ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ከህወሓት ጋር እንደሚደራደር መግለጹ ይታወሳል።
አፍሪካ ህብረት “ሰላም ሊያመጣ አይችልም” አስከማለት ደርሶ ነበረው ህወሓትም ቢሆን፤ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በሚካሄደው የሰላም ድርድር ሂደት ውስጥ ለመሳተፍ ዝግጁ መሆኑን ማስታወቁም ይታወሳል።