በባህር ዳር ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ከባድ ጦርነት መከሰቱን ነዋሪዎች ተናገሩ
በከተማዋ ባንኮችን ጨምሮ የግል እና የመንግስት ተቋማት ዝግ እንደሆኑም ተገልጿል
የክልሉ መንግስት በበኩሉ የጸጥታ ሀይሎች በባህርዳር እና አካባቢው “ጽንፈኞችን” እያጸዱ ነው ብሏል
በባህር ዳር ከዛሬ ማለዳ ጀምሮ ከባድ ጦርነት መከሰቱ ተገለጸ፡፡
በአማራ ክልል መዲና ባህርዳር ዛሬ ማለዳ ጀምሮ ከባድ ተኩስ ሲካሄድ እንደነበር ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ለደህንነታቸው የሰጉ እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ የባህርዳር ከተማ ነዋሪ እንዳሉን ከሆነ ከዛሬ ማለዳ 12 ሰዓት ጀምሮ የተኩስ ድምጽ መስማታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በፍርሃት ቤት ውስጥ በራቸውን ዘግተው ቤተሰባቸውን ይዘው መቀመጣቸውን የነገሩን እኝህ ነዋሪ በተለይም እስከ ጠዋቱ 3 ሰዓት ድረስ በከባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ መካሄዱንም ተናግረዋል፡፡
ውጊው በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል መካሄዱን እርግጠኛ ነኝ የሚሉን እኝህ ነዋሪ ንጹሃን ከቤታቸው ባለሙውጣታቸው የከፋ ጉዳት እንዳላስተናገዱም አክለዋል፡፡
አሁን ላይ በተለይም ከምሳ ሰዓት ጀምሮ የውጊያ ድምጽ እየሰሙ እንዳልሆነ አንቡላንሶች በመንገዶች ላይ ሲመላለሱ መመልከታቸውንም ነግረውናል፡፡
ሌላኛው በባህር ዳር መሀል ከተማ ነዋሪ መሆናቸውን እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ከሌሊት ጀምሮ የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ለመግባት ጥቃት መክፈታቸውን ሰምቻለሁ ሲሉ ነግረውናል፡፡
በተለይም በተለምዶ አየር ሀይል ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ በአባይ ማዶ እና ቀበሌ 14 በኩል የፋኖ ታጣቂዎች ወደ ከተማዋ ገብተዋል መባሉን እንደሰሙ የነገሩን እኝህ አስተያየት ሰጪ ከመንግስት የጸጥታ ሀይሎች ጋር ከባድ ውጊያ ሲካሄድ ማርፈዱን ጠቅሰዋል፡፡
አሁን ላይ የመንግስት እና የግል ተቋማት ከጠዋት ጀምሮ እንደተዘጉ፣ ከአንቡላንስ እና የጸጥታ ተቋማት ተሽከርካሪዎች በስተቀር በመንገዶች ላይ ምንም አይነት ተሽከርካሪ እንደሌለም ይህ አስተያየት ሰጪ አክሏል፡፡
የአማራ ክልል ሰላምና ደህንነት ሀላፊ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በባህር ዳርን ጨምሮ በክልሉ ስላለው የጸጥታ ሁኔታ እንዲነግሩን ላቀረብንላቸው ጥያቄ “አሁን ላይ ለሌላ ስራ ከክልሉ ውጪ ነኝ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተውናል፡፡
ይሁንና የክልሉ ኮሙንኬሽን ቢሮ ዛሬ ጠዋት ላይ ባወጣው መግለጫ በባህርዳር እና በክልሉ የጸጥታ ሀይሎች “ጽንፈኞችን” እያጸዱ ነው፣ ባህርዳር ከተማና አካባቢዉ ከጽንፈኛ ቡድኑ ጸድተዋል ብሏል፡፡
በአማራ ክልል በመከላከያ የተገደሉባቸውን ቤተሰቦቻቸውን መቅበር የተከለከሉ አሉ - አምነስቲ
የመከላከያ ሰራዊት እና የክልሉ የጸጥታ ሀይልም ህግ የማስከበር ስራዉን በተሟላ ሁኔታ እየተገበረ እንደሚገኝ የገለጸው የአማራ ክልል ኮሙንኬሽን ቢሮ እነዚህ የጸጥታ ሀይሎች የክልሉን ሰላም ሙሉ በሙሉ ወደነበረበት ለመመለስ በጥሩ ቁመና ላይ እንደሆኑም በመግለጫው ላይ ጠቅሷል፡፡
ከ2015 ዓ/ም ሚያዚያ ወር ጀምሮ የፌደራል መንግስት የክልል ልዩ ሀይሎችን መልሼ አደራጃለሁ የሚል ውሳኔ ካሳለፈበት ጊዜ ጀምሮ በአማራ ክልል በመንግስት የጸጥታ ሀይሎች እና ፋኖ ታጣቂዎች መካከል ጦርነት መከሰቱ ይታወሳል፡፡
ይህ ጦርነት እየሰፋ መምጣቱን ተከትሎ በክልሉ ከሀምሌ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለስድስት ወራት የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የታወጀ ሲሆን አዋጁ ለተጨማሪ አራት ወራት መራዘሙ አይዘነጋም፡፡