ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በተለይም አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ የሁለቱንም ተፋላሚ ኃይሎች በጂዳ በማገኛነት ጥረት አድርገው ነበር
የሱዳኑ ሄሜቲ በጅቡቲ በታቀደው ንግግር ላይ እንደማይገኙ ማሳወቃቸው ተገለጸ።
ከሱዳን ጦር ጋር እየተዋጉ ያሉት የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች መሪ ጀነራል መሀመድ ሀምዳን ደጋሎ ወይም ሄሜቲ በጅቡቲ እንደማይገኙ ማሳወቃቸውን ምንጮች ገልጸዋል።
ሄሜቲ ለምን መገኘት እንደማይፈልጉ ምክንያታቸውን ገልጽ አላደረጉም።
የሱዳን ጦር መሪ እና የሉአላዊ የሽግግር ምክርቤቱ ፕሬዝደንት ጀነራል አልቡርሃን በጅቡቲ ከመሀመድ ደጋሎ ወይም ሄሜቲ ጋር በሚቀጥለው ሀሙስ እንዲገኙ በኢጋድ ኃላፊ የግብዣ ደብዳቤ መጋበዛቸው ተዘግቦ ነበር።
ውይይቱ እንዲደረግ ከኢጋድ እና ከአፍሪካ ህብረት በተጨማሪ አሜሪካም ጫና አድርጋ የነበረ ቢሆንም፣ ሄሜቲ እንደማይገኙ ማሳወቃቸው እውን እንዳይሆን ያደርገዋል።
ከባለፈው ሚያዝያ አጋማሽ ጀምሮ የተቀሰቀሰው ጦርነት 9ሺ ሰዎች እንዳገዱ እና ከስድስት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑ ሰዎች እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል።
ጦርነቱን በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት በተለይም አሜሪካ እና ሳኡዲ አረቢያ የሁለቱንም ተፋላሚ ኃይሎች በጂዳ በማገኛነት ጥረት አድርገው ነበር።
ነገርግን ድርድሩ መፍትሄ ሳያመጣ ሊቋረጥ ችሏል።
ዲፕሎማቶች ድርድሩ ያልተሳካው ሁለቱም ኃይሎች እንደሚያሸንፉ ግምት በመውሰዳቸው ነው ይላሉ።
ሱዳንን ለሶስት አስርት አመታት የመሩት ኦመር ሀሰን አልበሽር በህዝባዊ ከመጽ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ በሱዳን በጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ የሚመራ የሲቪል አስተዳደር ተቋቁሞ ነበር።
ነገርግን የሱዳን ጦር ጀነራሎች በጠቅላይ ሚኒስትር ሀምዶክ አስተዳደር ላይ መፈንቅለ መንግሰት አድርገው ስልጣን በብቸኝነት ተቆጣጠሩ።
ይህን ተከትሎ ወታደራዊ ስልጣን ያየዙት ጀነራል ቡርሃን እና ሄሜቲ በመካከላቸው ግጭት ተቀስቅሶ፣ ሀገሪቱ ቀውስ ውስጥ ገብታለች።