ምክር ቤቱ በመጪው ሳምንት ከጉባዔው የደረሰውን የውሳኔ ሃሳብ ያያል
“የውሳኔ ሃሳብ ወደ ምክር ቤቱ የሚመጣው ህገ መንግስታዊ ትርጉም ያስፈልገዋል ሲባል ብቻ ነው”-የምክር ቤቱ ቃል አቀባይ
አባላቱንም ሰኔ 3 እና 4 እንዲሰበሰቡ ጠርቷል
በጉባዔው የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ ለማየት ምክር ቤቱ አባላቱን ለመጪው ሳምንት ጠራ
ከህገ መንግስት ትርጉም ጋር በተያያዘ ከህገ መንግስት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ የደረሰውን የውሳኔ ሃሳብ ለማየት አባላቱን ለመጪው ሳምንት ሰኔ 3 እና 4 መጥራቱን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ፡፡
የውሳኔ ሃሳቡ ለምክር ቤቱ መድረሱን ያረጋገጡት የምክር ቤቱ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረስላሴ የውሳኔ ሃሳቡ በቅድሚያ በምክር ቤቱ የህገ መንግስት ትርጉምና ማንነት ጉዳይ ቋሚ ኮሚቴ የሚታይ እንደሆነ ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
ለዚህም ቋሚ ኮሚቴው በመጪው ሳምንት የመጀመሪያ ቀናት ይሰበሰባል ያሉ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናት ማለትም ሰኔ 3 እና 4 ቀን 2012 ዓ/ም ለሚሰበሰቡት የምክር ቤቱ አባላት ጥሪ እየተደረገ ይገኛልም ብለዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ጉባዔው አቀረብኩ ያለው የውሳኔ ሃሳብ ምን የሚል እንደሆነ አል ዐይን ላቀረበላቸው ጥያቄ ዝርዝር መረጃው የለኝም ነው ያሉት፡፡
ሆኖም የውሳኔ ሃሳቡ ወደ ምክር ቤቱ የሚመጣው ህገ መንግስታዊ ትርጉም ያስፈልገዋል ሲባል ብቻ እንደሆነ አልሸሸጉም፡፡
“ጉባዔው ትርጉም አያስፈልገውም ካለ ራሱ ምላሽ ይሰጣል፤ያስፈልገዋል ካለ ደግሞ ወደ እኛ [ወደ ምክር ቤቱ] ይልካል፡፡ አሁንም የውሳኔ ሃሳቡን የላከው ቢያስፈልገው ነው ማለት ነው፡፡ ነገር ግን ዝርዝር ጉዳዮችን ማየት ያፈልጋል፤ [እኔ] ይሄን አላየሁም ቋሚ ኮሚቴው ነው የያዘው”ሲሉም ነው ስለጉዳዩ ያስቀመጡት፡፡
በጉባዔው የተላከው የውሳኔ ሃሳብ ምንም ይሁን ምን ቋሚ ኮሚቴው አስፈላጊነቱን ካመነበት የህዝብ እና የምሁራንን አስተያየት የማድመጥ፣ትርጉም የማያስፈልገውም ከሆነ የመወሰን ስልጣን አለው፡፡
ነገር ግን “ከአሁን ቀደም በምሁራን እና በባለሙያዎች ደረጃ ሰፊ ውይይት ስለተካሄደበት ቋሚ ኮሚቴው ይህን ላያደርግ ይችላል፤ይህ የሚወስነውም በራሱ ነው” እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ፡፡
“ምን ሊወስን እንደሚችል አላውቅም እርግጠኛም አይደለሁም”ም ብለዋል፡፡
ምክር ቤቱ በቋሚ ኮሚቴው በኩል በሚቀርብለት ዝርዝር ሃሳብ ላይ ከተወያየ በኋላ የደረሰበትን የመጨረሻ የውሳኔ ሃሳብ ጉባዔው ውሳኔውን ባስታወቀ በአንድ ወር ውስጥ ይፋ ያደርጋልም ብለዋል ዳይሬክተሩ፡፡