ሃውቲዎች 30 ሚሊየን ዶላር የሚያወጣ የአሜሪካ ድሮን መትተው መጣላቸውን ገለጹ
የቡድኑ ቃል አቀባይ “ኤምኪው-9” ድሮኑ በማሪብ ግዛት መመታቱን ቢያስታውቁም፥ ዋይትሃውስ እስካሁን ማረጋገጫ አልሰጠም
ኢራን የየመኑ ቡድን ድሮኖችን መትቶ የሚጥልበት “358” የተሰኘ ሚሳኤል ማስታጠቋ ይናገራል
የየመኑ ሃውቲ በሀገሪቱ ሲበር የነበረ የአሜሪካን ትልቅ ሰው አልባ አውሮፕላን (ድሮን) መትተው መጣላቸውን አስታወቁ።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ በተቀረጸ የቪዲዮ ምስል “ኤምኪው-9” ድሮኑ በማሪብ ግዛት መመታቱን ተናግረዋል።
ቡድኑ የተመታውን ድሮን የሚያሳይ ምስል ባይለቅም ከዚህ ቀደም በነበረው ልምዱ በቀናት ውስጥ በይፋ እንደሚለቀው ይጠበቃል።
የአሜሪካ ጦር በሃውቲዎች የቀረበውን መረጃ ቢያውቀውም እስካሁን “የደረሰኝ ሪፖርት የለም” ሲል ለአሶሼትድ ፕረስ ገልጿል።
ሃውቲዎች በ2014 መዲናዋን ሰንአ ከተቆጣጠሩ ጀምሮ ጀነራል አቶሚክስ የሚያመርተውን “ኤምኪው-9” ድሮኖች በተደጋጋሚ መትተው ጥለዋል።
የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህም የአሜሪካውን ግዙፍ ድሮን ደጋግመው መጣላቸው ይታወቃል።
የቡድኑ ቃል አቀባይ ያህያ ሳሬ ዛሬ ማለዳ ተመትቶ ስለወደቀው ድሮን ዝርዝር ማብራሪያን አልሰጡም።
ይሁን እንጂ ኢራን የየመኑ ቡድን ድሮኖችን መትቶ የሚጥልበት “358” የተሰኘ ከምድር ወደ ሰማይ የሚምዘገዘግ ሚሳኤል ማስታጠቋ ይናገራል።
ኢራን ክሱን ብትቃወምም በየመን የጦር ሜዳዎች ሚሳኤሎችን ጨምሮ በርካታ ቴህራን ሰራሽ የጦር መሳሪያዎች መገኘታቸውን አሶሼትድ ፕረስ ያወሳል።
በቴህራን ሚሳኤል እንደተመታ የሚታመነው የአሜሪካው የስለላ ድሮን “ኤምኪው-9” 30 ሚሊየን ዶላር ያወጣል።
ከ15 ሺህ ሜትር በላይ ከፍታ ለ24 ስአት መብረር እንደሚችልም መረጃዎች ያመላክታሉ።
ሃውቲዎች የዋሽንግተንን ድሮን መምታታቸውን ካሳወቁ በኋላ አሜሪካ በየመኗ ኢብ ከተማ የአየር ጥቃት መፈጸሟን የቡድኑ ንብረት የሆነው አል ማሲራህ ቴሌቪዥን ዘግቧል።