የየመን አየር መንገድ ከ6 ዓመት በኋላ የመጀመሪያውን የመንገደኞች በረራ አካሄደ
በረራው የተከናወነው የተመድ አደራዳሪነት ለሁለት ወር የተኩስ አቁም ለማድረግ በመስማማታቸው ነው
በዚህ በረራ ላይ 137 መንገደኞች ከየመን መዲና ሰነዓ ተነስተው ኦማን አርፈዋል
የእርስ በርስ ጦርነት ባየለባት የመን ከስድስት ዓመት በኋላ የመጀመሪያውን የመንገደኞች በረራ አስተናግዳለች።
በእርስ በርስ ጦርነት እየታመሰች ባለችው የመን የሀገሪቱ አየር መንገድ የመንገደኞች በረራ ካቆመ ስድስት ዓመት ሆኖታል።
አየር መንገዱ በረራ ያቆመው በሀገሪቱ ባጋጠመው የእርስ በርስ ጦርነት ምክንያት ሲሆን፤ ከስድስት ዓመት በኋላ የመጀመሪያውን የመንገደኞች በረራ አድርጓል፡፡
ይህ የመንገደኞች በረራ የተካሄደው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በየመን የእርስ በርስ ጦርነት እያካሄዱ ባሉት የሀውሲ አማጺያን እና በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅና በተሰጠው የየመን መንግስት መካከል ድርድር ከተካሄደ በኋላ ነው።
ተመድ ባካሄደው በዚህ ድርድር መሰረት ሁለቱም ወገኖች የተኩስ አቁም በማድረግ የሰብዓዊ ድጋፍ የለምንም ገደብ እንዲደርስ ተስማምተዋል።
በዚህ ስምምነት መሰረትም የየመን አየር መንገድ 137 መንገደኞችን ከሀገሪቱ ሰነዓ አውሮፕላን ጣቢያ ተነስቶ በጆርዳን መዲና ኦማን እንዳረፉ ሮይተርስ ዘግቧል።
የሰነዓ አውሮፕላን ጣቢያ በፈረንጆቹ 2016 ላይ በየመን እርስ በርስ ጦርነቱ አይሎ የሀውሲ አማጺያን ሰነዓ ከተማን መቆጣጠሩን ተከትሎ ነበር ለመንገደኞች የበረራ አገልግሎት እንዳይሰጥ ታግዶ ቆይቷል።