በኤደን ባህረሰላጤ በሚሳኤል የተመታች መርከብ በእሳት መያያዟ ተሰማ
የሚሳኤል ጥቃቱን የየመኑ ሃውቲ ታጣቂ ቡድን ሳይፈጽመው እንዳልቀረ ቢገመትም እስካሁን ሃላፊነቱን አልወሰደም
ሃውቲዎች የእስራኤልና ሃማስ ጦርነት ከተጀመረ ወዲህ በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ ከ50 በላይ ጥቃቶችን ፈጽመዋል
በኤደን ባህረሰላጤ በሚሳኤል የተመታች መርከብ በእሳት መያያዟ ተሰማ።
የሚሳኤል ጥቃቱን የየመኑ ሃውቲ ታጣቂ ቡድን ሳይፈጽመው እንዳልቀረ ተገምቷል።
የብሪታንያው የማሪታይም ንግድ አስተዳደር ተቋም በእሳት የተያያዘችው መርከብ ንብረትነቷ የማን እንደሆነ ይፋ አላደረገም።
አምብሬይ የተባለው የግል የደህንነት ተቋም የንግድ መርከቧ በሚሳኤል መመታቷን መርከበኞች በጭንቅ ውስጥ ሆነው በሬዲዮ መልዕክት መላካቸውን ገልጿል።
ተቋሙ ከማሌዥያ ወደ ጣሊያኗ ቬኒስ ስትጓዝ የነበረችው መርከብ “በሃውቲዎች ኢላማ ከተደረጉት ውስጥ ናት” ከማለት ውጭ በየትኛው ሀገር እንደምትተዳደር ይፋ አላደረገም።
ከዚህ ጥቃት በኋላም በየመን የወደብ ከተማዋ ሆዴይዳ አቅራቢያ ሁለተኛ የሚሳኤል ጥቃት መፈጸሙን የብሪታንያው የማሪታይም ንግድ አስተዳደር ቢገልጽም ማብራሪያ አልሰጠም ብሏል አሶሼትድ ፕረስ በዘገባው።
ጥቃቶቹን አድርሷል በሚል የተጠረጠረው ሃውቲ እስካሁን ሃላፊነቱን አልወሰደም።
መዲናዋን ሰንአ ጨምሮ አብዛኛውን የሀገሪቱን ክፍል የተቆጣጠሩት ሃውቲዎች እስራኤል በጋዛ ጦርነት ከጀመረች ወዲህ በቀይ ባህር በሚጓዙ ከእስራኤልና አጋሮቿ ጋር የተገናኙ መርከቦች ላይ ጥቃት በማድረስ ላይ ናቸው።
በቀይ ባህር በሚጓዙ መርከቦች ላይ ከ50 በላይ ጥቃቶችን ያደረሰው ቡድኑ ሶስት መርከበኞችን መግደሉ፤ አንድ መርከብ በቁጥጥር ስር ማዋሉና አንድ መርከብ ማስመጡ ይታወሳል።
አሜሪካ እና ብሪታንያ አጋሮቻቸውን በማስተባበር ከጥር ወር ወዲህ በየመን የቡድኑ ይዞታዎች ላይ በፈጸሟቸው የአየር ድብደባዎችም ከ46 በላይ ተዋጊዎችና ንጹሃን መገደላቸውን ቡድኑ መግለጹ አይዘነጋም።
ከእስራኤል፣ አሜሪካ እና ብሪታንያ ጋር የተያያዙ መርከቦች ላይ ጥቃት በማድረስ ለፍልስጤማውያን አጋርነቱን እየገለጸ የሚገኘው የሃውቲ ቡድን፥ እስራኤል በጋዛ የምትፈጽመውን “ጭፍጨፋ” ካላቆመች ጥቃቱን እንደማያቆም በተደጋጋሚ ገልጿል።